የኢትዮጵያ የዘመን መጽሐፍ ካሁን በኋላ የጠብመንጃና የጉልበት ታሪክን አይመዘግብም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2018 ዓ.ም (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የዘመን መጽሐፍ ካሁን በኋላ የጠብመንጃና የጉልበት ታሪክን አይመዘግብም አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ለ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመት ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ÷ ሀገራዊ ምክክሩ ገደ መልካም መሆኑን በምክክሩ ብቻ ሳይሆን በውጤቱም እያሳየ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም በአዲስ ዓመት ዋዜማ በ100ዎች የሚቆጠሩ ታራሚዎችን መንግሥት በምሕረት እንዲፈቱ አድርጓል ነው ያሉት።
ታራሚዎቹ በምህረት እንዲፈቱ የተደረገበት ምክንያት የሀገራዊ ምክክሩን ውጤት በፍቅር፣ በይቅርታና በሰላም ለመጀመር በማሰብ እንደሆነ ገልጸዋል ፡፡
በምክክሩ ወቅት ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል እስረኞች እንዲፈቱ የሚል ጥያቄ እንደነበር ጠቁመው ÷ መንግሥትም ለምክክሩ ሐሳቦች ትግበራ ያለውን ቁርጠኝነት በዚህ የይቅርታ ሒደት ማሳየት መጀመሩን አረጋግጠዋል፡፡
በዚህ የይቅርታ ሒደት የተፈቱ ወገኖች በሀገራዊ ምክክር ምክረ ሐሳቦች ላይ አዎንታዊ ሚና ይጫወታሉ ተብሎ እንደሚታመን አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የዘመን መጽሐፍ ካሁን በኋላ የጠብመንጃና የጉልበት ታሪክን አይመዘግብም ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
መነጋገር፣ መከራከርና መፎካከር ሲቻል ግጭትና ጦርነት አዋጪ አይደለም ፤የብዕርና የሐሳብ ጊዜ እንጂ የጠብመንጃ እና የጉልበት ጊዜ አልፏል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፡፡