Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት መሰረታዊ የሸቀጦችን የገበያ ዋጋ ለማረጋጋት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ጳጉሜን 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዘጠና ዓመት የንግድ ሥራ ልምድ ያለው የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት አዲሱን የ2019 የዘመን መለወጫ እና መጪ በዓላትን ምክንያት በማድረግ የሸቀጦችን ዋጋ ለማረጋጋትና የአቅርቦት ክፍተቶችን ለመሙላት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው፡፡
ድርጅቱ የደንበኞቹን ፍላጎት መሠረት በማድረግ በተለይም መሠረታዊ የምግብ እና የንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን እንዲሁም አልባሳትን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ በማቅረብ ላይ ይገኛል።
ከሚያሰራጫቸው ምርቶች መካከል ፈሳሽ የምግብ ዘይት፣ በተለያየ መጠን የታሸገ የዳቦ ዱቄት፣ ስኳር፣ ፓስታ፣ መኮረኒ፣ አንሶላና ብርድ ልብሶች እንዲሁም የጽዳት ሳሙናዎች ይገኙበታል።
እነዚህን የፍጆታ ሸቀጦች በአዲስ አበባ እና በክልሎች በሚገኙ ከ80 በላይ የሽያጭ ቅርንጫፎቹ በኩል ለህብረተሰቡ እያከፋፈለ መሆኑን ተመላክቷል፡፡
ድርጅቱ የህብረተሰቡን መሠረታዊ ፍላጎቶች መነሻ በማድረግ ጥራት ያላቸውን ምርቶች በማቅረብ፤ በገበያው ላይ የሚታየውን የዋጋ ግሽበትና የአቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል።
በተጨማሪም ድርጅቱ በአግሮ-ፕሮሰሲንግ፣ በጨርቃጨርቅ እና በቆዳ ዘርፎች ለተሰማሩ አምራች ኢንተርፕራይዞች የተለያዩ የግብዓት ምርቶችን እያቀረበ ይገኛል።
ከእነዚህም መካከል የድርና ማግ ምርቶችን በማምረት ለሀገር ባህል አልባሳት አምራቾች በማቅረብ የግብዓት አቅርቦት ችግራቸውን ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነ አመልክቷል።
በአሁኑ ሰዓት ድርጅቱ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች አድማስ በማስፋት በዘመናዊ ማሽኖችና ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች በመታገዝ ለከባድ፣ መካከለኛና ቀላል ተሽከርካሪዎች የብቃት ማረጋገጫ አገልግሎትን በተመጣጣኝ ዋጋ በመስጠት ላይ ይገኛል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.