Fana: At a Speed of Life!

ዕድል ማግኘት፡ የዲጂታል ኢትዮጵያ ተጨባጭ ማሳያዎች

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት “እርሷ አልተቀየረችም፤ የተቀየረው ዕድል ማግኘቷ ነው” ሲሉ በዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞ ውስጥ የአንዲት ሴት ነጋዴን የዲጂታል ጉዞ ሽግግር የሚያሳይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ቴክኖሎጂና ምቹ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ በእያንዳንዱ ዜጋ ሕይወት ውስጥ የሚመጣውን ተጨባጭና መዋቅራዊ ለውጥ የሚያሳይ ግልጽ ማሳያ ነው።
 
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት በዓለም መነጽር ከእውነተኛ አቅሟ ይልቅ በወቅታዊ ፈተናዎቿ ብቻ ስትመዘን ቆይታለች።
 
ታዲያ ከለውጡ ማግስት የመደመር መንግሥት በየዘርፉ ተግባራዊ ባደረገው የፖሊሲና የመዋቅር ሪፎርም ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛል።

የመደመር መንግሥት ከአምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ውስጥም ቴክኖሎጂን በማካተት የዲጂታል መሠረተ ልማትን በማስፋፋት ብሎም ብሔራዊ የዲጂታል ስትራቴጂዎችን በመንደፍ የኢትዮጵያ የዲጂታል ዓለም አዲስ መነቃቃት እንዲፈጥር አድርጓል።
 
በዚህም ዛሬ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ቀደም ሲል ሊደርሱባቸው የማይችሏቸውን የቴክኖሎጂ እና የኢኮኖሚ ዕድሎች በእጃቸው ማግኘት የጀመሩበት አዲስ ምዕራፍ እየተጻፈ ይገኛል።

ይህ  ለውጥ በአጋጣሚ የመጣ ሳይሆን መንግሥት በከፍተኛ ቁርጠኝነትና ስልታዊ በሆነ መንገድ በጀመረው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የመጣ ቀጥተኛ ውጤት ነው።

የዚህ ብሔራዊ ለውጥ መነሻ ውስጥ ደግሞ አንዱ ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታዋን በይፋ የመራችበት “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” የተሰኘው ስትራቴጂ ነው።

ይህ ስትራቴጂ ግብርናን፣ ማኑፋክቸሪንግን፣ ቱሪዝምንና የዲጂታል ገበያን የመሳሰሉ ቁልፍ የኢኮኖሚ ምሰሶዎችን በቴክኖሎጂ በማዘመን የዜጎችን ሕይወት ለመቀየር ትልቅ መሠረት ጥሏል።

በዚህ ስትራቴጂ አማካኝነት የተዘረጋው የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳ) እና የቴሌኮም ዘርፉ መከፈት ለሀገሪቱ የዲጂታል ጉዞ ትልቅ የመቀስቀሻ ሞተር መሆን ችሏል።

በዚህ መሠረት ቀደም ሲል ከመደበኛ የባንክ ሥርዓት ውጭ የነበሩ አነስተኛ ነጋዴዎች፣ ወጣቶች እና ዜጎች ዛሬ የዲጂታል ክፍያና የኢ-ኮሜርስ ቀጥተኛ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።

እንደ ቴሌብር እና ሲቢኢ ብር ያሉ የዲጂታል ፋይናንስ አማራጮች ዜጎች የራሳቸውን የፋይናንስ ታሪክና ዓለም አቀፋዊ አመኔታ እንዲገነቡ ሲያግዟቸው፣ ዛሬ ላይ ዜጎች ካሉበት ሳይንቀሳቀሱ በኦንላይን የሚገበያዩበትና ምርቶቻቸውን የሚያስተዋውቁበት የኢ-ኮሜርስ ዕድል በሰፊው እየተለመደ መጥቷል።

ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ለኢትዮጵያ የዲጂታላይዜሽን ጉዞ ማሳያነት ፥ ቀደም ሲል ከባንክ ሒሳብ፣ ከብድር ታሪክና ከመደበኛ የፋይናንስ ሥርዓት ውጭ ትሠራ የነበረች አነስተኛ ነጋዴ ሴት፤ በብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ከተመዘገበች በኋላ የዲጂታል ክፍያዎችን በመጠቀም የፋይናንስ ታሪክና አመኔታ መገንባት መቻሏን አስረድተው “እርሷ አልተቀየረችም፤ የተቀየረው ዕድል ማግኘቷ ነው” ሲሉ ያብራሩት።

በአሁኑ ወቅት የፓስፖርት ዕድሳት፣ የንግድ ፈቃድ ማውጣት፣ የትራፊክ ቅጣት ክፍያ እና የግብር አሰባሰብ ሥርዓቶች ሙሉ በሙሉ በዲጂታል መተግበሪያዎች መከናወናቸው ዜጎች ረጅም ሰልፍና እንግልት ሳይገጥማቸው አገልግሎታቸውን በቤታቸው ሆነው እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።

ኢትዮጵያ የጀመረችው የዲጂታል ጉዞ የዜጎችን ሕይወት ከማቅለል ባለፈም ለዜጎች በርካታ የፋይናንስ በሮችን ይከፍታል።

እንዲሁም የመንግሥትን አሠራር ግልጽ፣ ፈጣን እና ከቢሮክራሲ የጸዳ ለማድረግ ጉልህ አበርክቶ አለው።

ኢትዮጵያ ይህንን “የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” ስትራቴጂ ስኬት መሠረት በማድረግ ወደ “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030” የረጅም ጊዜ የዲጂታል ርዕይ በልበ ሙሉነት ተሸጋግራለች።

የ2030 ዕቅድ ትኩረቱን ሙሉ በሙሉ እንደ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI)፣ ቢግ ዳታ (Big Data) እና የሳይበር ደህንነት ባሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ላይ የሚያደርግ ነው።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ማዕከል ለመሆን የምታደርገው ጉዞ መጪውን ትውልድ በዲጂታል ዘመን ዕውቀት አስታጥቆ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ለማሸነፍ ዝግጁ የሚያደርግ የዕድገት ምሰሶ ነው።

በሶስና አለማየሁ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.