Fana: At a Speed of Life!

ብርሃናማው ቀን መስረከም አንድ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 1፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ዛሬ መስከረም አንድ ነው፡፡ አንድ የምንለው ግን ለቀን መቁጠሪያ ብቻ አይደለም፤ ለአዲስ ጅምር ለአዲስ ተስፋ ለአዲስ ስኬትም ነው።
ዛሬ በሀገራችን አራቱም ማዕዘን የደስታና የአዲስ ተስፋ ስሜት ሰፍኗል፤ ህዝቡ በባህል አልባሳት አጊጧል፤ መስኩ አደይ አበባ ለብሷል።
ማለዳ በየሰፈሩ የእንቁጣጣሽ ተናፋቂ ዜማ ይሰማል በለመለመ ቀጤማ በተጎዘጎዙ ቤቶች ውስጥ የተቆላ ቡና መዓዛ ያውዳል።
ከየደጃፉ የሚደመጡት ቆየት ያሉ እንዲሁም አዳዲስ የበዓል ዘፈኖች ትውልድን በሚያስተስር የጋራ ትዝታ አስረው ስሜትን ሰቅዘው ይዘው ይመጣሉ።
አበባየሆሽ እያሉ ለሚጨፍሩ ልጃገረዶች ጎረቤቶችም ስጦታ እና እውነተኛ ፈገግታ ያካፍላል። ይህም ትልቁ የሰው ልጅ ሀብት ፍቅር መሆኑን ያስታውሰናል።
ዛሬ በሮች ሁሉ ክፍት ናቸው። የተራራቁ ወዳጆች ይጠያየቃሉ ልጆች የአባቶችንና የእናቶችን ጉልበት ስመው ምርቃት ይቀበላሉ፤ ማዕድ ቀርቦ ይቋደሳሉ የአዲስ ዘመን ምኞታቸውንም በአሜን ያሳርጋሉ፡፡
የኢትዮጵያውያንን በዓል አከባበር ልዩ የሚያደርገው የመረዳዳት እና የደስታ ተካፋይነት መንፈስ ከጥንት ህዝቡ የተጋመደበት መሆኑ ነው፡፡
በኢትዮጵያውያን የማህበረሰብ ህይወት ባህል መሰረት፤ ዛሬ የትኛውም ጎረቤት ማዕዱ ባዶ ሆኖ እንዳያድር ሁሉም በአቅሙ ይተጋገዛል።
ይህ መልካም እሴት እንዲህ ባለ የበዓላት ወቅት ብቻ ሳይሆን በአዘቦቱም በሰፊው ህዝብ ዘንድ ባህል ሆኖ ከትላንት እስከ ዛሬ የኢትዮጵያውያን መገለጫ መሆኑን ማሳያ ነው።
የመደመር መንግሥትም ማዕድ በማጋራት፣ ስጦታዎችን በማበርከት እና ለተቸገሩ እጁን ዘርግቶ አለኝታነቱን በማሳየት አርአያነት ያለው የማዕድ ማጋራት ተግባር እየፈጸመ ይገኛል፡፡
በዛሬው እለትም እንደወትሮው ሁሉ በበዓል ያለውን ተካፍሎ በመተሳሰብ ማሳለፍ ከሚጋራው ማዕድም በላይ፤ የኢትዮጵያውያንን የመተሳሰብና የአብሮነት መንፈስ የሚያጎናጽፍ የመልካምነት መገለጫ ነው፡፡
ይህ አዲስ ዓመትም በይቅርታ በአንድነት እና በጋራ ርዕይ የድካማችንን ፍሬ የምንበላበት ይሁንልን፤ ሰላም እና ፍቅርን ያብዛልን።
መልካም አዲስ ዓመት!
በምሕረት ደምሴ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.