ወጣቱ ትውልድ የኢትዮጵያን የወደፊት ዕድል መቅረጽ በሚያስችሉ ክህሎቶች መገንባት አለበት – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለ2019 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ለመላው የትምህርት ማሕበረሰብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ፥ በመላው ሀገራችን ለሚገኙ ተማሪዎቻችን አዲሱ የትምህርት ዘመን ስኬታማ እንዲሆን እመኛለሁ ብለዋል።
ወጣቱ ትውልድ ለኢትዮጵያ ትልቁ ሃብቷ በመሆኑ የ2019 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ጅማሮን ተከትሎ፤ እያንዳንዱ ተማሪ ለላቀ እውቀት በትጋትና ጉጉት ትምህርቱን መከታተልና ለጥሩ ውጤት በጽናት መትጋት አለበት ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ወጣቱ ትውልድ የሀገራችንን የወደፊት ዕድል መቅረጽ በሚያስችሉ ክህሎቶች መገንባት እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ዛሬ እየተገበርናቸው ያሉ በርካታ የልማት ሥራዎች የነገን ትውልድ ታሳቢ ያደረጉ በመሆናቸው፣ ወጣቶች ደግሞ የዚህ ቀጣይ ዕድል ተጠቃሚና ባለአደራ እንደመሆናችሁ መጠን፣ የኢትዮጵያን ታላቅ የስልጣኔ ታሪክ ወደፊት ለማስቀጠል የእናንተ ቁርጠኝነት መሠረት እንደሆነ ሙሉ እምነቴ ነው ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ብቁ እና በራሱ የሚተማመን ትውልድ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የመምህራን ትጋት እና መሰጠት መሰረታዊ ምሰሶ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡
መምህራን ተማሪዎቻችንን ማነቃቃት፣ አቅማቸውን ማውጣት እንዲሁም ነገ ተፎካካሪ ሆነው እንዲወጡ የሚያስችሏቸውን ዕውቀት፣ ክህሎትና እሴቶችን የማስታጠቅ አደራን ቀጥሉበት ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በትምህርት ዘርፉ ውስጥ ለሚገኙ ባለድርሻ አካላት በሙሉ ስኬታማ እና ፍሬያማ የትምህርት ዘመን እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል፡፡