በብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያ ያሳካችው ድል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓለም አቀፍ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ውስጥ ፈጣንና ግዙፍ ተጽዕኖ እያሳደገ የመጣው ብሪክስ፤ ሀገራት ሁለገብ ጥቅሞቻቸውን የሚያስከብሩበትና ስትራቴጂካዊ ግንኙነቶቻቸውን የሚያጠናክሩበት ቁልፍ መድረክ ሆኗል።
ኢትዮጵያ በኒው ዴልሂ በተካሄደው በ18ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ያደረገችው ንቁና ውጤታማ ተሳትፎ ኢትዮጵያ በባለብዙ ወገን እና በሁለትዮሽ ዲፕሎማሲ መስክ የተቀዳጀችውን አዲስ ከፍታ በግልጽ ያሳየ ነው፡፡
ጉባኤው ኢትዮጵያ ያሳካቻቸውን ሀገራዊ ስኬቶች እንድታሳይ እድል የፈጠረ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በውይይት ጠረጴዛ ላይ ያላትን የመደራደር አቅም በእጅጉ አሳድጎታል።
ኢትዮጵያ በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ በወጣው የኒው ዴልሂ ዲክላሬሽን ውሳኔዎች ውስጥ መካተቷ የዲፕሎማሲ ጥረቷ ትልቅ ማሳያ ነው።
በተለይም በዲክላሬሽኑ ውስጥ ኢትዮጵያ የዓለም የፋይናንስ ተቋማትን በአባልነት ለመቀላቀል የምታደርገው ጥረት ድጋፍ ማግኘቷ እና በዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ካውንስል ውስጥ አህጉሯን በመወከል እንድትቀመጥ የተሰጣት እውቅና የውጭ ፖሊሲዋ ያስገኛቸውን ስትራቴጂካዊ ድሎች የሚያሳዩ ናቸው።
እነዚህ ውሳኔዎች የሀገሪቱን የኢኮኖሚና የንግድ ፍላጎቶች ከማስጠበቅ ባሻገር፤ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ ግዙፍ ተቋማት በዓለም አቀፍ ደህንነትና መመዘኛዎች ዙሪያ በሚደረጉ ውሳኔዎች ላይ የጎላ ተፅዕኖ እንዲኖራቸው በር ይከፍታሉ።
ከዚሁ ጎን ለጎን ኢትዮጵያ የራሷን ሀገራዊ ጥቅም ከማስከበር ባለፈ ለተቀረው የአፍሪካ አህጉር ድምጽ በመሆን በግንባር ቀደምትነት ሞግታለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው ላይ ያቀረቧቸው ሀሳቦች የብሪክስን አጀንዳዎች ከአፍሪካ ህብረት የአጀንዳ 2063 ዘላቂ ልማት፣ ሰላምና ደህንነት ግቦች ጋር የሚያስተሳስሩ ነበሩ።
ይህም ኢትዮጵያ ለአህጉራዊ ትስስርና ለደቡብ ደቡብ ትብብር ያላትን ቁርጠኝነት ከመግለጽም በላይ አህጉራዊ ውክልናዋን የበለጠ አጠናክሮታል።
በጉባኤው ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ፣ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና ከሌሎች ሀገራት መሪዎች ጋር ያደረጓቸው ውይይቶች በዲፕሎማሲው ዓለም ትልቅ ትርጉም የሚሰጣቸው ናቸው።
ኢትዮጵያ በብሪክስ ጉባኤ ያሳየችው ተሳትፎ የዓለምን የዲፕሎማሲ ሚዛን ጠብቃ በመጓዝ ላይ መሆኗን ያረጋገጠ ነው።
አሁን ያለው ተግባራዊ ዲፕሎማሲ ሀገሪቱ ከነባር አበዳሪዎችና ፋይናንስ ተቋማት ጋር ያላትን ግንኙነት ሳይጎዳ እንደ ኒው ዲቨሎፕመንት ባንክ ያሉ አዳዲስ የፋይናንስ አማራጮችን እንድትጠቀም እድል ፈጥሮላታል።
ይህ አቀራረብ ፈተናዎችንና ተለዋዋጭ የዓለም አቀፍ ፖለቲካ ሁኔታዎችን ተሻግሮ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ጂኦ ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ከፍ የሚያደርግ ትክክለኛ የውጭ ግንኙነት መስመር መሆኑን ያስመሰከረ ነው።
በዮናስ ጌትነት