የዲጂታል ፍርድ ቤት ፍትህን የበለጠ ግልጽና ተደራሽ ለማድረግ ወሳኝ ምዕራፍ ነው – የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት
አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የዲጂታል ፍርድ ቤት አሰራር ፍትሃዊና ግልጽ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ወሳኝ ምዕራፍ ነው አሉ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት።
በድሬደዋ አስተዳደር ፍርድ ቤቶችን ከወረቀት ንክኪ የፀዳ የዲጂታላይዜሽን አገልግሎት ማስጀመሪያ ሥነ ስርዓት ዛሬ ተካሂዷል።
በሥነ ስርዓቱ ላይ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት እንዳሉት ÷ የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ትግበራው የፍትህ ስርዓቱን ተደራሽ፣ ግልፅና ውጤታማ በማድረግ የህዝብ እርካታን ለማረጋገጥ እያስቻለ ይገኛል።
የፍርድ ቤቶች አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ ማድረግ ተገልጋዮች ባሉበት ቦታ ሆነው ጉዳያቸውን የሚከታተሉበትን ስርዓት ለመዘርጋት እንዳስቻለም ተናግረዋል።
በተለይ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውስጥ የተጀመረውን የስማርት ኮርት ስርዓት በመላው አገሪቱ በማስፋት ፈጣንና ግልፅ አገልግሎት በማስፈን የተገልጋዩን እርካታ ለማረጋገጥ ማስቻሉን ገልጸዋል።
የፍርድ ቤቶችን መረጃ አያያዝ ለማዘመን ተግባራዊ የተደረጉ የዲጂታል አገልግሎቶችም ፈጣንና ተደራሽ ፍትህን ለማስፋት እንዳስቻሉም አብራርተዋል።
የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው÷ የፍርድ ቤቶችን አሰራር ዲጂታላይዝ ማድረግ ፍትህን በእኩልነት፣ በግልፅነት እና በቅልጥፍና ተደራሽ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በአሁኑ ወቅትም ፍርድ ቤቶች ከወረቀት ንክኪ የጸዳ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት የተገልጋዩን እርካታ ለማረጋገጥ እየሰሩ ስለመሆኑም አንስተዋል።