Fana: At a Speed of Life!

የሕዝብ ድምጽ የሥልጣን ምንጭነት በተግባር ሲረጋገጥ

በአፍሪካና በኢትዮጵያ ረጅም የታሪክ አድማስ ውስጥ የሕዝብ ድምጽ የመንግሥት ሕልውናና የፍትሕ መሠረት ሆኖ ቆይቷል።
በባህላዊው አስተዳደራችን አበው ከትልቅ ዛፍ ጥላ ሥር ተሰብስበው ሀገር የሚያድኑበት፣ በቃል ኪዳንና በጋራ ምክር ውሳኔ የሚያሳልፉበት ሥርዓት ነበራቸው።
አፍሪካውያን «ብቸኛ ዛፍ በነፋስ ይወድቃል፤ በጫካ ውስጥ ያሉ ዛፎች ግን እርስ በርስ ይደጋገፋሉ» እንደሚሉት ሁሉ፣ የትኛውም አስተዳደርና መንግሥት ዘላቂ የሚሆነው በሕዝብ ድምጽና በጋራ ድጋፍ ላይ ሲመሠረት ብቻ ነው።
ኢትዮጵያ የቀደመ ሥልጣኔና የረጅም ዘመን የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ታሪክ ባለቤት ናት። ከአክሱም ገናና ሥልጣኔ እስከ ዛግዌ፣ ከጎንደር እስከ ሸዋ፣ ከገዳ ሥርዓት እስከ ሐረርና ሸዋ ሱልጣኔቶች በዘለቀው የሀገረ መንግሥት የታሪክ አድማስ ውስጥ የኢትዮጵያ መንግሥት ሕልውና በአባቶች ጽናትና መሥዋዕትነት የተገነባ ነው።
አፍሪካውያን፤ «ዛፍ እንደ ቅርንጫፎቹ ሁሉ ሥሩም ጥልቅ ነው» እንደሚሉት፣ የዛሬዋ ኢትዮጵያ የመንግሥት ምሥረታ ሒደት የዚያ ታሪካዊ መሠረት ውጤት ቢሆንም፣ የሥልጣን ምንጩ ግን ከሰይፍ ወደ ሕዝብ ድምጽ ተሸጋግሯል።
የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ማክስ ዌበር የመንግሥትን ሕጋዊነት ሲያስረዱ÷ ‹‹ዘመናዊ መንግሥት ሕጋዊ የሚሆነው በሕዝብ ነፃ ፈቃድና በሕግ የበላይነት መሠረት ሲዋቀር ነው፤›› ይላሉ።
በኢትዮጵያ የታሪክ ጉዞ ውስጥ ለዘመናት የቆየውን የመንግሥት ምሥረታ ሥርዓት ወደ ዘመናዊ ዴሞክራሲያዊ መንገድ ለማሸጋገር የተደረጉ ጥረቶች በርካታ ፈተናዎች የነበሩባቸው ቢሆንም በሒደት የሕዝብ ተሳትፎን ማዕከል ያደረገ ባህል እየጎለበተ መጥቷል።
ዛሬ ላይ ስንደርስ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት መጠናቀቁ የዚሁ ረጅም የልማድና የለውጥ ጉዞ ማሳያ ነው። በምርጫው 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ 10 ሺህ 438 ዕጩዎች እና ከ54 ሚሊየን በላይ መራጮች ተሳትፈዋል፡፡ ሒደቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና ለሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ያለውን የፀና ፍላጎት በተግባር ያረጋገጠበትም ነው።
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 56 መሰረት በምክር ቤቱ አብላጫ ወንበር ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት የፌዴራሉን መንግሥት ሕግ አስፈጻሚ አካል እንደሚያደራጅና እንደሚመራ ይደነግጋል። የአዲሱ መንግሥት ምሥረታና የምክር ቤቱ መከፈቻ ሥነ ሥርዓት መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም ይከናወናል፡፡
የመንግሥት ምስረታው የሀገራዊ ምክክር ሒደት በስኬት ከተጠናቀቀ በኋላ የሚካሄድ መሆኑ ለኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው፡፡
ይህ የመንግሥት ምሥረታ ከትናንቱ የሥልጣን አመጣጥ ባህል ጋር ሲነፃፀር ትልቅ የታሪክ ምዕራፍ ነው፤ የሥልጣን መነሻውም ሆነ መድረሻው የሕዝብ ውሳኔ መሆኑን ያበስራል።
ሀገራዊ እድገትና ዘላቂ ሰላም እውን የሚሆነው በመላው ሕዝብ ህብረትና ንቁ ተሳትፎ ነው፤ በሕዝብ የተመረጠው መንግሥትም በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ሀገርና ሕዝብን የመምራት ኃላፊነቱን ሲረከብ ይህንኑ አጠቃላይ የሕዝብ ፍላጎት መሠረት በማድረግ ይሆናል።
የሚመሠረተው መንግሥት የታሪካችንን ገናናነት ከዘመናዊ ዴሞክራሲያዊ አሠራር ጋር በማጣመር፣ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ እድገትና አንድነት መረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ይጠበቃል።
በተረፈ ወርቁ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.