Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት አማካኝነት የቱሪዝም ሀብቷን ለማልማት እየሰራች ነው – ሰላማዊት ካሳ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት አማካኝነት የቱሪዝም ሀብቷን ለማስተዋወቅ እና ለማልማት እየሰራች ነው አሉ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፡፡

ሚኒስትሯ መስከረም 17 ቀን 2019 ዓ.ም የሚከበረውን የዓለም የቱሪዝም ቀን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ÷ የሰው ሰራሽ አስተውሎት በጎብኝዎች ፍላጎት ላይ የተመሰረተ እንዲሁም ጥራት ያለው እና የተደራጀ መረጃን በማጋራት የቱሪዝም ሀብትን እያስተዋወቀ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያም በሰው ሰራሽ አስተውሎት አማካኝነት የቱሪዝም ሀብቷን በአግባቡ ለመጠቀም እየሰራች እንደምትገኝ ገልጸው በዛሬው ዕለትም ሚኒስቴሩ የቱሪስት መረጃ መስጫ ማዕከል ማስመረቁን ተናግረዋል።

ይህ የቱሪስት መረጃ መስጫ ማዕከል በዲጂታል ፕላትፎርም በመታገዝ ጥራት ያለው መረጃ ለጎብኝዎች ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስችልም አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም የቪዚት ኢትዮጵያ ዌብሳይት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን እንዲጠቀም በማድረግ የተደራጀ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጓል ብለዋል።

አያይዘውም በመስከረም ወር በኢትዮጵያ የሚከበሩ በዓላትን የበለጠ ለማስተዋወቅ እና ለማልማት የተለያዩ ዝግጀቶች መደረጋቸውንም አመልክተዋል፡፡

ለአብነትም በዓላቱን ምክንያት በማድረግ የጥበብ ሥራ ውድድሮች፣ ከአዲስ አበባ ቤኑና መንደር የደርሶ መልስ የባቡር ጉዞ እንዲሁም በጎንደር አብያተ መንግሥት “ህይወት በአብያተ መንግስት” የተሰኘ ዝግጅት እንደሚካሄድም ተናግረዋል፡፡

በተጠናቀቀው 2018 በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ የውጭ ጎብኚዎች ኢትዮጵያን የጎበኙ ሲሆን÷ ከዘርፉም ከ5 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።

አፈጻጸሙ ከ2017 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከ300 ሺህ በላይ ጎብኚዎች እና ከ21 በመቶ በላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ጭማሪ ማሳየቱን አብራርተዋል።

የኮንፈረንስ ቱሪዝምን ለማሳደግ በተደረገው ጥረት ቀደም ሲል በአዲስ አበባ በዓመት ከ30 እስከ 40 ይካሄዱ የነበሩ ዓለም አቀፍ ሁነቶች ወደ 220 ማደጋቸውን አመልክተዋል፡፡

በቅድስት አባተ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.