የሉዓላዊነት ምልክት፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ለዘጠኝ አሥርት ዓመታት ያህል የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በማስከበር ረገድ የማይተካ ታሪካዊ ሚና ሲጫወት ቆይቷል፤ አሁንም እተጫወተ ይገኛል፡፡
ተቋሙ በተለያዩ ዘመናት የተጋረጡበትን ውስብስብ ፈተናዎች በጽናት በማለፍ፣ ለሀገር ድንበር መከበርና ለሕዝብ ደህንነት ሲል የከፈለውን ከፍተኛ መስዋዕትነት ውጤት በማስጠበቅ እስከ ዛሬ ድረስ የኢትዮጵያ የሰማይ ላይ ጋሻ ሆኖ ዘልቋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል የተመሰረተበትን 90ኛ ዓመት “የኢትዮጵያ አየር ኃይል የነጻነትና የአንድነት ምልክት” በሚል መሪ ቃል ባከበረበት ወቅት እንደተገለጸው፣ ይህ ታላቅ ተቋም የሀገርን ሉዓላዊነት የሚያስከብር ከመሆኑም በላይ ለመላው የአፍሪካ አህጉር የጽናትና የኩራት ማሳያ ሆኖ ያገለግላል።
በቅርብ ዓመታት በተካሄዱት አጠቃላይ የማሻሻያና የመልሶ ግንባታ ሥራዎች ተቋሙ ከፍተኛ የቴክኖሎጂና የሰው ኃይል አቅም መገንባት ችሏል፡፡
አየር ኃይሉ የላቁ ተዋጊ አውሮፕላኖችን፣ ዘመናዊ የራዳርና የአየር መከላከያ ሥርዓቶችን፣ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እንዲሁም በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተደገፉ የስልጠና መድረኮችን በማጣመር ወደ አራተኛ ትውልድ የጦር መሳሪያ ቴክኖሎጂ አቅም ተሸጋግሯል፡፡
በቀጣይም እስከ ፈረንጆቹ 2030 ድረስ ወደ አምስተኛው ትውልድ የጦር መሳሪያ የቴክኖሎጂ ደረጃ ለማደግ በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋነኛ ዓላማ ጥቃትን የመከላከልና ሰላምን የማስከበር አቅምን ማጎልበት ቢሆንም፤ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት የሚደፍር ማንኛውም ጠላት ሲገኝ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታውን በብቃት ለመወጣት ሁልጊዜም በሙሉ ዝግጁነት ላይ ይገኛል።
ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሀገርን ድንበር ከመጠበቅ ባሻገር በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በተካሄዱ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ በንቃት በመሳተፍ ለአህጉራዊ ሰላምና ጸጥታ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
በአሁኑ ወቅት ከሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገትና ከዘመናዊ ዲፕሎማሲ ጋር ተጣጥሞ እያደገ የሚገኘው አየር ኃይሉ፣ የኢትዮጵያን የአየር ክልል በቀንና በሌሊት ንቁ ሆኖ በመጠበቅ የሀገሪቱን ታሪካዊና ሕገ መንግሥታዊ ሉዓላዊነት በአስተማማኝ ሁኔታ በመጠበቅ ላይ ይገኛል።
በመሆኑም ዘመናዊ የመከላከያ አቅሙን፣ የሰው ኃይል ክህሎቱንና አህጉራዊ ተጽዕኖውን ያሳደገው የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሀገርን ሰላም የሚያረጋግጥ፣ የኢትዮጵያን የነጻነት ታሪክ የሚያስቀጥልና ለወደፊቱም የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም አጽንቶ የሚያቆይ ጠንካራ መከታ ሆኖ ይቀጥላል።
በአብረሃም አበራ