Fana: At a Speed of Life!

የከተማ ልማት የነዋሪዎችን የኑሮ ክብር በሚጠብቅ መልኩ መከናወን አለበት – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የከተማ ልማት የነዋሪዎችን የኑሮ ክብር በሚጠብቅ መልኩ መከናወን አለበት አሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመልሶ ማልማት የተገነባውን የቅጠል ተራ የመኖሪያ ቤት በዛሬው ዕለት ለነዋሪዎች አስተላልፈዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ከተማ ለነዋሪዎች የተሻለ ኑሮ፣ ክብርና ምቹ የአኗኗር ሁኔታ የሚፈጥር ሥፍራ መሆን አለበት፡፡
በቅጠል ተራ 960 ቤቶችን በአራት ወር ውስጥ ገንብተን ከቦታው ላይ ለተነሱ ነዋሪዎች መልሰን አስተላልፈናል ነው ያሉት፡፡
ቅጠል ተራ ለመኖር እጅግ ምቹ ያልነበረ፤ ለሰው ልጅ ክብር የማይመጥን፤ እጅግ የቆሸሸ፣ የተፋፈገ እና የተጨናነቀ በመሆኑ የሰው ህይወትም በአስከፊ ሁኔታ በእሳት አደጋ ያጣንበት አካባቢ ነበር ሲሉም አስታውሰዋል።
ዘመናዊና ሁሉንም ነገር የተሟሉላቸው ባለ 9 ወለል የሆኑ ብዛታቸው 9 ህንጻዎች፤ 960 ቤቶች ተገንብተው ወደ ምቹ መኖሪያ አካባቢ መቀየራቸውን ገልጸዋል፡፡
“የመርካቶ የበጎነት የመኖሪያ መንደር” በ11 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ የተገነቡ G+8 የሆኑ ዘጠኝ ብሎኮች በአጠቃላይ 960 ቤቶች ያሉት ሲሆኑ፣ ሰፊ የስራ እድልን የሚፈጥሩ 371 የንግድ ሱቆች በውስጡም የህጻናት የመጫወቻ ስፍራ፣ የስፓርት ማዘውተሪያመ፣ የኳስ ሜዳ፣ ቅርጫት ኳስ፣ የእጅ ኳስ፣ የመረብ ኳስ እና የሰውነት ማጎልመሻ ቦታዎች መሰራታቸውን አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም ለነዋሪዎች የመኪና ማቆምያ ፓርኪንግ፣ ለኤሌክትሪክ መኪና ቻርጅ ማድረጊያ፣ የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገድ፣ ዘጠኙም ብሎኮች ላይ የጋራ መጠቀሚያ ሰገነት፣ ሊፍት፣ የፍሳሽና የኤሌክትሪክ መስመሮች በዘመናዊ መልክ ተሟልተው መገንባታቸውን አመልክተዋል፡፡
ይህ በመርካቶ የበጎነት የመኖሪያ መንደር የሰው ህይወትን የሚቀይር መርካቶ አካባቢን “ተራ” በሚል ስያሜ የተሰጣቸው ቅጠል ተራ፣ ጭድ ተራ፣ ገብስ ተራ፣ ሳር ተራ እና ቦንብ ተራ ጎስቋላ አካባቢዎችን ወደ ውብ አካባቢ የመለወጥ ጉልህ ማሳያ ነው ብለዋል።
ነዋሪዎች የክብር ኑሮ እንዲኖሩ ህይወታቸውን የሚቀይሩ ተግባራትን ያለ እረፍት በመፈጸም ነዋሪዎች አዲስ ህይወት እንዲጀምሩ ማድረግ ነው ተችሏል ብለዋል።
ከተማችን ውብና ፅዱ፤ ለነዋሪዎቻችን የተመቸች ከተማ እንድትሆን ያለ እረፍት የመስራት ተግባራችን ይበልጥ አጠናክረን ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ስራ ላይ ለተሳተፉት አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በግዛቸው ግርማዬ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.