Fana: At a Speed of Life!

የጽናትና የጀግንነት ምልክት፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገር ድንበር ሲደፈር፣ የህዝብ ሰላምና ህልውና በጠላት ሴራ ሲፈተን፣ በግንባር ቀደምነት ደረቱን ሰጥቶ፣ ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሶ ሀገር የሚያቆም ታላቅ ኃይል አለ እሱም የሀገር መከላከያ ሰራዊት ነው።
ሰራዊቱ የሚከፍለው ዋጋ ለግል ጥቅም ወይም ለጊዜያዊ ክብር ሳይሆን፤ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ህልውና እና ለህዝቧ ነጻነት ነው።
በተለያየ ዘመን የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለመድፈር የተነሱ የውስጥና የውጭ ጠላቶችን ሴራ በማክሸፍ፤ ሀገርን በመከራ ውስጥ አጽንቶ የማሻገር ጥበቡ የዚሁ ተቋም መለያ ምልክት ነው።
መከላከያ ሰራዊቱ የሀገር አለኝታ፣ የሰላም ዘብ እና የኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊ አንድነት ማህተም ነው።
ለወዳጆቹ ጠባቂ፣ ለጠላቶቹ ደግሞ አይበገሬ በመሆን፤ ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷ እና በነጻነቷ ጸንታ እንድትቆም አድርጓል።
የሰራዊቱ ተልዕኮ በጦር ሜዳ ውጊያ ብቻ የተወሰነ አይደለም። በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ወቅት ከህዝብ ጎን በመቆም፤ የዜጎችን ህይወት የመታደግና የልማት ስራዎችን የመደገፍ ህዝባዊ ወገንተኝነቱ አሳይቷል፡፡
ዘመን ያፈራውን ቴክኖሎጂ እና የውጊያ ብቃቶች በመታጠቅ ራሱን በየጊዜው የሚያድስ፣ የሰለጠነና የተደራጀ ዘመናዊ ሰራዊት ነው።
በሀገር ውስጥ ተልዕኮው ብቻ ሳይሆን፤ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር መድረኮች ላይ ያሳየው ታላቅ የዲሲፕሊንና የብቃት ደረጃ የኢትዮጵያን ገጽታ በበጎ መልኩ ያስጠራ ነው።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለሀገሩ ታማኝ፣ ለህዝቡ አጋር ደግሞ ሆኖ የቆመ ታላቅ ዘብ ነው።
የታሪክ ባለቤት፣ የዛሬው ዘብ እና የነገው የሰላም ዋስት የሆነው መከላከያ ሰራዊት ሀገርን የመጠበቅና የማጽናት ታሪካዊ አደራውን በጽናት መወጣቱን ይቀጥላል።
በእመቤት ሲሳይ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.