ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በ81ኛው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ያነሷቸው ዋና ዋና ነጥቦች On Sep 24, 2026 56 ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት መሥራች አባል እንደ መሆኗ መጠን ዛሬ የምንገኝበትን ዓለም አቀፍ ድርጅት ለመመስረት የበኩላችንን ሚና በመጫወት የጋራ ጸጥታ አስከባሪዎች ሆነን በጽናት ቆመናል። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዓለም አቀፍ ግጭቶችን እና የጦርነት አደጋዎችን ለመከላከል የሚያስችሉትን ተስማሚ ሐሳቦች በድጋሚ በጽናት እንዲያጠናክር እንጠይቃለን። ዓለም አቀፍ ግጭቶችን እና ጦርነቶችን ለመከላከል የሀገራት የጋራ ትብብር እና ሉዓላዊ እኩልነት ወሳኝ ነው። አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ የአየር ንብረት ቀውስ እና እየሰፋ የመጣው የሀብት አለመመጣጠን ፖሊሲ ብቻ ሳይሆኑ የሰው ልጆችን ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ ናቸው። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችሉ በቂ ሃብቶች ቢኖረውም ችግሮችን መፍታት ያልተቻለው የተግባር ርምጃዎችን በቁርጠኝነት መፈጸም ባለመቻሉ ነው። የተባበሩት መንግስታት እጅግ ከባድ የሆኑ ፈተናዎችን ተጋፍጦ አስደናቂ ድሎችን አስመዝግቧል፤ ነገር ግን ይህ በቂ አይደለም። ከመጠን ያለፈ የነዳጅ ፍጆታ በአሁኑ ጊዜ ፕላኔታችንን እየጎዳ ይገኛል፤ ይህም የህይወት መጥፋት እና የመሠረተ ልማት ውድመትን እያስከተለ ነው፤ ይህን ቀውስ ለመፍታት ከፈለግን አሁኑ ርምጃ መውሰድ አለብን። ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2027 የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባኤን (COP32) ታስተናግዳለች፤ የዓለም መሪዎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በዚህ አስፈላጊ ጉባኤ ላይ እንድትሳተፉ እጋብዛለሁ። አፍሪካ በዓለም አቀፍ ውሳኔ አሰጣጥ ላይ እንደ ጥላ ሆና ቆይታለች፤ 1 ነጥብ 6 ቢሊየን አፍሪካውያን በዓለም መድረክ እኩል ውክልና የማግኘት መብት ይገባቸዋል። ኢትዮጵያ በመሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ በንግድ እና በምስራቅ አፍሪካ ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ትብብርን እና ውህደትን ለማጠናከር በትጋት እየሠራች ነው። በውስጥ ጉዳያችን ላይ የጠላት አካላት ጣልቃ ገብነት ምንም እንኳ ቢቀጥልም በአፍሪካ ውስጥ የበለጸጉና በፍጥነት እያደጉ ከሚገኙ ሀገራት አንዱ ለመሆን በቅተናል። ኢትዮጵያ ፍትሃዊ እና ነጻ ምርጫ በማካሄድ ጠንካራ የዴሞክራሲ መሰረት ጥላለች፤ እንዲሁም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ አዲስና ዲሞክራሲን ያጠናከረ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ማካሄድ ችላለች። የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድም ኢትዮጵያ ከውጭ ጥገኝነት ወደ ትልቅ የስንዴ አምራችነት መሸጋገር ችላለች፤ ራሷንም መመገብ እንደምትችል አሳይታለች። ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ዓመታት ባከናወነችው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር 56 ቢሊየን ዛፎች የተተከሉ ሲሆን በዚህም በዓመት 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ሜትሪክ ቶን የካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀትን ለመቆጣጠር ታስቧል። የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለአፍሪካ የንጹህ ኃይል ፕሮጀክት ነው፤ የውሃ ሃብት የጋራ ብልጽግና እድገትን የሚያመጣ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት 12 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር የሚፈጅ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እየገነባ ነው ፤ይህም በዓመት 110 ሚሊየን ተጓዦችን የማስተናግድ አቅም አለው። ኢትዮጵያ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ አስተማማኝ የባህር በር ማግኘት ወሳኝ በመሆኑ ይህንን ፍላጎቷን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማግኘት እየሰራች ነው። በሶስና አለማየሁ 56 Share FacebookTwitterTelegramWhatsAppEmailViberPrint