ኢትዮጵያ አንድነቷን ስታጠናክርና መንግስቷም ጠንካራ ሲሆን ህዝቦቿ ይከበራሉ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ አንድነቷን ስታጠናክር፣ ሰላሟን ስታረጋግጥና መንግስቷም ጠንካራ ሲሆን ህዝቦቿ ይከበራሉ አሉ የኢንተርናሽናል ዳያስፖራ ማህበር አመራሮች።
የኢንተርናሽናል ዳያስፖራ ማህበር ፕሬዚዳንት ኢድሪስ መሐመድ እንዳሉት፥ የውጭ ሀገር ነዋሪ ኢትዮጵያውያን በሀገር ጉዳይ ላይ ያላቸውን ሚና ለማጠናከር ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው።
ዲያስፖራው በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ያደረገው ተሳትፎ የሀገር ጉዳይ ላይ በጋራ መስራት የሚቻልበት ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል።
አሁንም በኢትዮጵያ እየተከናወኑ የሚገኙ እንደ ቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ዓይነት ትልልቅ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ የዲያስፖራው ማህበረሰብ የበኩሉን ለመወጣት ቁርጠኛ መሆኑን አስረድተዋል።
የዲያስፖራው አቅም በእውቀትና ሙያ ሽግግር፣ በኢንቨስትመንትና በሌሎች የልማት ዘርፎች በማሳተፍ ለሀገር ግንባታ የሚያበረክተውን ሚና ማስፋት እንደሚገባም ገልጸዋል።
የማህበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ሰለሞን አሻግሬ በበኩላቸው፥ ህዝብና መንግስት እጅና ጓንት ሆነው በጋራ መስራት እንደሚገባቸው እና የተጀመሩ የልማትና የሀገር ግንባታ ሥራዎች ሳይቋረጡ ቀጣይነታቸው እንዲጠበቅ ጠይቀዋል።
በተለይም መንግስት ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍ ጠንካራ መንግስታዊ ተቋም መገንባት ላይ ትኩረቱን ማድረግ እንዳለበትም ጠቁመዋል።
ሀገር ስትጠናከር፣ ሰላሟ ሲረጋገጥና መንግስቷ ከህዝቧ ጋር በጋራ ሲሰራ የሁሉም ዜጎች ተጠቃሚነትና ክብር ሊረጋገጥ እንደሚችልም ነው ያስረዱት።
የሀገር ጥንካሬ ከመንግስት ብቻ የሚመነጭ ሳይሆን ከጠንካራ ህዝብ፣ ከሰላምና ከአንድነት ጋር የተሳሰረ መሆኑን ገልጸው ጠንካራ መንግስት ጠንካራ ህዝብ የያዘ ማለት እንደሆነ አስረድተዋል።
ሀገርና መንግስት ሲጠናከሩ ትውልድን የሚያሻግር የመንግስት ግንባታ ሊፈጠር እንደሚችልም ገልጸው የአገልግሎት ዘርፉን ይበልጥ ማሻሻል፣ ዜጎችን የሚያጨናንቁ አሰራሮችን ማስወገድና የተሳለጠ አገልግሎትን ማስፋፋት በቀጣይ በትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል።
በዮናስ ጌትነት