ኢኮኖሚን እንደ ብሔራዊ ኃይል፡ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የከፍታ ጉዞ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 25፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በዘመናዊው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ እና ጂኦ-ፖለቲካዊ ውድድር ውስጥ የሀገራት ጥንካሬና አካባቢያዊ ተጽዕኖ የሚወሰነው በወታደራዊ አቅም ብቻ ሳይሆን በጠንካራ ኢኮኖሚያዊ መዋቅር፣ ራስን በመቻል እና በቴክኖሎጂ ዝግጁነት ነው።
በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የታየው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ዘርፎች ሽግግር ኢኮኖሚያዊ ብልጽግናን የሀገር ህልውና እና የከፍታ ማረጋገጫ አድርጎ የመቅረጽ ሂደት ላይ ያተኮረ ነው።
ይህ ጉዞ በዋናነት በመደመር ፍልስፍና የተቃኘ ሲሆን፣ የቀደሙ አዎንታዊ እሴቶችን በማስቀጠል፣ የታዩ ስህተቶችን በማረም እና የነገዋን ሀገር ተስፋ ብሩህ ለማድረግ አዳዲስ አሰራሮችን በመተግበር ላይ የተመሰረተ ነው።
የኢኮኖሚ አቅምን እንደ ብሔራዊ ኃይል የመጠቀም ዋነኛው ማሳያ ትውልድ ተሸጋሪ የሆኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ ማጠናቀቅ ነው።
ለዓመታት ተጀምረው ሲጓተቱ የቆዩ ወይም በዕቅድ ላይ የነበሩ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ወደ ፍፃሜ ማሸጋገር ተችሏል። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረትና የሉዓላዊነት ማረጋገጫ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ህያው ታሪካዊ አብነት ነው። የተጓተተውን የግድቡን ግንባታ በማጠናቀቅ ሥራ ማስጀመር ተችሏል፡፡
ኢትዮጵያ በቅርቡ ይፋ ያደረገችው የተፈጥሮ ጋዝ እና የማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክት፣ ሀገሪቷ የተፈጥሮ ሀብቷን ተጠቅማ ወደ አዲስ የኢንዱስትሪ እና የግብርና ምዕራፍ መሸጋገሯን ያበሰረ ታላቅ የብሔራዊ ኩራት ሆኗል።
ይህ ግዙፍ የልማት ሥራ በከፍተኛ ወጪ ከውጭ የሚገባውን የማዳበሪያ በሀገር ውስጥ በማምረት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የኢኮኖሚ ነፃነትን ለማወጅ የሚጫወተው ሚና የጎላ ነው።
በተጨማሪም አየር መንገዳችን በአቪዬሽን ዘርፍ የአህጉራዊ መሪነቱን አስጠብቆ ለማስቀጠል በቢሾፍቱ የሚገነባው ዘመናዊ የአውሮፕላን ማረፊያ ሀገሪቱ ታላላቅ እቅዶችን አቅዳ ወደ ተግባር የመቀየር የጽናት አቅሟን የሚያረጋግጥ ነው።
በምግብ እህል ራስን አለመቻል የሀገርን ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ክብር ከሚያዳክሙ ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ ነው። በግብርናው ዘርፍ በተካሄደው መሰረታዊ የፖሊሲና የተግባር ለውጥ፣ ከዚህ ቀደም በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ ይገባ የነበረውን የስንዴ ምርት በሀገር ውስጥ ሙሉ በሙሉ መተካት ተችሏል። ከዚህም አልፎ የስንዴ ምርትን ወደ ውጭ ሀገራት መላክ ተጀምሯል፡፡
በመደመር እይታ ኢንደስትሪዎችን በተበታተነ ሁኔታ ከመገንባት ይልቅ የተሻለ የመሰረተ ልማት እና የአገልግሎት ማዕከል ባላቸው የኢንደስትሪ ፓርኮች እና ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ማደራጀት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል።
የኢንደስትሪ ፓርኮች የውጭ ኢንቨስተሮችን በመሳብ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማምጣት እና ለዓለም አቀፍ ገበያ የሚላኩ ምርቶችን በማብዛት እና ጥራት በመጨመር የውጭ ምንዛሪ ግኝትን አሳድገዋል። ኢንዱስትሪዎቹ ለስራ ዕድል ፈጠራ ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡
የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤና የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም ለኢኮኖሚ ዘላቂነት መሠረት ናቸው። በአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ በቢሊየኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል የአፈር መሸርሸርን መከላከልና የደን ሽፋንን መልሶ ማልማት ተችሏል።
ይህ ህዝባዊ ንቅናቄ ኢትዮጵያን በአካባቢ ጥበቃና በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ረገድ በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች አርአያ ያደረገ ግዙፍ ስኬት ነው።
ኢኮኖሚን በማዘመን ረገድ የቴክኖሎጂ ሚና ከፍ ያለ ነው። የ”ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025″ ስትራቴጂካዊ እቅድ በስኬት መጠናቀቁን ተከተሎ ወደ “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030” የተደረገው ሽግግር የሀገሪቱን የንግድና የአገልግሎት ምህዳር በፍጥነት እየቀየረው ይገኛል።
ተግባራዊ የሆኑ የተለያዩ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶች መስፋፋት የንግድ እንቅስቃሴውን ቀልጣፋ፣ ዘመናዊ እና ግልጽ አድርገውታል።
ከተሞችን ለኑሮና ለቱሪዝም ምቹ ማድረግ የኢኮኖሚ ማነቃቂያ ቁልፍ መሣሪያ ነው። በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ እና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የተካሄደው የኮሪደር ልማት የከተሞችን ገጽታ ከመቀየሩም በላይ ለነዋሪዎች ምቹ የመኖሪያ አካባቢን፤ ለጎብኚዎችም ሳቢና ማራኪ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡
በሌላ በኩል፣ ሀገሪቱ ያላትን ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ፀጋዎች ወደ ኢኮኖሚ ሀብት ለመቀየር እንደ ወንጪ፣ ጎርጎራ እና ኮይሻ ባሉ አካባቢዎች የተገነቡት የቱሪዝም መዳረሻዎች እና መሰረተ ልማቶች የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪዝም ፍሰትን በእጅጉ እያነቃቁት ነው።
በመደመር እይታ በመሠረተ ልማት፣ በግብርና፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እና በአካባቢ ጥበቃ ዘርፎች የተከናወኑት ተግባራት አጠቃላይ ድምር ውጤት፤ ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ከፍታዋን እንድታረጋግጥ የሚያስችሉና የብሔራዊ ኩራት ምንጭ የሆኑ ስኬቶች ናቸው።
የኢትዮጵያውያንን እውቀት፣ ጥረት እና የታላቅነት ህልም በተግባር የገለጹት እነኝህ ስኬቶች፤ በራስ አቅም ሀገራዊ እቅዶችን ዳር ማድረስ እንደሚቻል ለዓለም ያረጋገጡ ከመሆናቸውም በላይ ለቀጣዩ ትውልድ ትልቅ ተስፋ እና መነቃቃትን የፈጠሩ የፅናት ዐሻራዎች ናቸው።
በመልካም ፈቃዱ