Fana: At a Speed of Life!

ከአፍሪካ አንድነት ርዕይ ጋር የተሳሰረው የኢትዮጵያና ናይጄሪያ ግንኙነት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አፍሪካ በታሪኳ የተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዞዎችን ያሳለፈች አህጉር ናት። በዚህ ረጅም የአፍሪካ ታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያና ናይጄሪያ ልዩ ቦታ ያላቸው ሀገራት ናቸው።
በቅኝ ግዛት ዘመን ነጻነቷን ጠብቃ የቆየችው ኢትዮጵያ፤ እንዲሁም በ1960 ነጻነቷን ያገኘችው ናይጄሪያ፤ በአፍሪካ የነጻነት፣ የአንድነትና የልማት ትግል ውስጥ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።
የሁለቱ ሀገራት ዘመናዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሥር መሠረቱን በ1960ዎቹ ያደረገ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በ1961 በሌጎስ ኤምባሲዋን መክፈቷ በግንኙነቱ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ርምጃ ነበር።
በኋላም ናይጄሪያ በአዲስ አበባ የዲፕሎማሲያዊ ተወካይነቷን አጠናክራለች። የሁለቱ ሀገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት በ1960ዎቹ በይፋ መመሥረቱ የዛሬውን ግንኙነት መሠረት ጥሏል።
የኢትዮጵያና ናይጄሪያ ግንኙነትን ለመረዳት 1963 ልዩ ትርጉም አለው። በዚያ ዓመት 32 የነጻነት ሀገራት መሪዎች በአዲስ አበባ ተሰብስበው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (OAU) መሠረት ጣሉ። ኢትዮጵያና ናይጄሪያም ከመሥራች አባላቱ መካከል ነበሩ።
ይህ ክስተት ከሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት በላይ የሆነ ትርጉም ነበረው። ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጽ/ቤት መቀመጫ ሆና ስትቀጥል፣ ናይጄሪያም ከአህጉሪቱ ትልቁ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሀገራት አንዷ ሆና በአፍሪካ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ንቁ ሚና መጫወት ጀመረች።
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋና መቀመጫም በአዲስ አበባ እንዲሆን የተወሰነው በዚያው የመሥራችነት ሂደት ነበር።
በመሆኑም የኢትዮጵያና ናይጄሪያ ግንኙነት የሁለት መንግሥታት ግንኙነት ብቻ ሳይሆን፤ ከአፍሪካ አንድነት ርዕይ ጋር የተሳሰረ ግንኙነት ሆኖ ቆይቷል።
የሁለቱ ሀገራት ትብብር በዲፕሎማሲ ብቻ አልተወሰነም። በ1960ዎቹና 1970ዎቹ በርካታ የናይጄሪያ ወታደራዊ መኮንኖች በኢትዮጵያ በሚገኘው የሐረር ወታደራዊ አካዳሚ ሥልጠና አግኝተዋል። ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል የሙያና የልምድ ልውውጥ ቀደም ብሎ እንደነበር ያሳያል።
በትምህርት ዘርፍም ግንኙነቱ የራሱ ታሪክ አለው። በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ከናይጄሪያ የመጡ ተማሪዎች በአዲስ አበባ ትምህርት አግኝተዋል፤ በ2000 ደግሞ ናይጄሪያውያን መምህራን በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና ትምህርት ተቋማት እንዲያገለግሉ ስምምነት ተደርጓል። ይህ የደቡብ-ደቡብ ትብብር ግልጽ ምሳሌ ሆኗል።
ከ1990ዎቹ ጀምሮ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ አዲስ ደረጃ መሸጋገር ጀመረ። የመሪዎች ጉብኝት፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ውይይቶች፣ የትምህርትና የባህል ትብብር እየጨመረ መጣ።
በ2006 ሁለቱ ሀገራት የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን ወደ ሁለገብ ስትራቴጂክ አጋርነት ለማሳደግ ተስማሙ። ይህንንም ለማስፈጸም የጋራ ሚኒስትሮች ኮሚሽን ተቋቋመ።
ይህ መዋቅር በንግድ፣ በትምህርት፣ በግብርና፣ በባህል፣ በጤና፣ በደህንነትና በሌሎችም ዘርፎች ትብብርን ለማስፋፋት መድረክ ሆኗል።
ሁለቱ ሀገራት በብዙ ነገሮች ይመሳሰላሉ። ሁለቱም ብዙ ብሔርና ቋንቋዎች ያሏቸው ሀገራት ናቸው፤ ትልቅ የሰው ሀብት አላቸው፤ በአፍሪካ ፖለቲካ ላይም ጉልህ ድምፅ አላቸው። ይህ ተመሳሳይነት የሁለቱ ሀገራትን ልምድ ለመለዋወጥ ጠንካራ መሠረት ፈጥሯል።
በአፍሪካ ህብረትም ሁለቱ ሀገራት በአህጉራዊ ሰላም፣ ደህንነት፣ ልማትና የአፍሪካ ድምፅ በዓለም መድረክ እንዲጠናከር የሚያደርጉ ዋና ተዋናዮች ናቸው።
በ2017 የኢትዮጵያና ናይጄሪያ የጋራ ሚኒስትሮች ኮሚሽን ከ10 ዓመት በኋላ በአቡጃ ተካሄደ። በ2022 ደግሞ ሦስተኛው የጋራ ሚኒስትሮች ኮሚሽን በአዲስ አበባ ተካሄዶ፣ በወታደራዊ ጉዳይ፣ በጤና፣ በንግድ፣ በኢንዱስትሪ፣ በባህልና በስፖርት ዘርፎች የትብብር ስምምነቶች ተወያይተዋል።
የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትም በበረራ፣ በንግድ፣ በትምህርትና በባህል ልውውጥ እየተጠናከረ ነው።
እንዲሁም በ2026 የሁለቱ ሀገራት ውይይት ወደ የሕግና የፍትሕ ትብብር ዘርፍም ተስፋፍቷል። ሰኔ 2026 ኢትዮጵያና ናይጄሪያ የተፈረደባቸው ሰዎች ልውውጥ የሚመለከት ስምምነት መፈራረማቸው የግንኙነቱ አዲስ የትብብር መስክ መከፈቱን ያሳያል።
የኢትዮጵያና ናይጄሪያ ግንኙነት ያለፈውን ታሪክ በመጠበቅ ብቻ የሚቆም አይደለም። በሁለቱ ሀገራት ያለው የሰው ሀብት፣ የገበያ አቅም፣ የግብርና ልምድ፣ የኢንዱስትሪ አቅምና የቴክኖሎጂ ዕድገት በተገቢው ከተጣመረ ለሁለቱም ሀገራት ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ አህጉር ትልቅ ዕድል ሊፈጥር ይችላል።
በተለይም የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስርን ማሳደግ፣ የአየር ትራንስፖርትንና የሰዎች እንቅስቃሴን ማቀላጠፍ፣ በትምህርትና ቴክኖሎጂ የልምድ ልውውጥን ማስፋፋት እና በአፍሪካ ህብረት ውስጥ የጋራ አቋምን ማጠናከር የወደፊቱን ግንኙነት የበለጠ ወደፊት ሊያራምዱት ይችላሉ።
በአቤል ነዋይ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.