ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የመደመር መንግሥት የካቢኔ አባላትን ለእጩነት ሲያቀርቡ እንደመስፈርት ያነሷቸው ዋና ዋና ነጥቦች፦
👉 ለእያንዳንዱ የካቢኔ አባላት የትምህርት ዝግጅት አንዱ መስፈርት ቢሆንም ነገር ግን ትምህርት ብቻውን ከመፈጸም አቅም ውጪ ሊታይ ስለማይገባው የመፈጸም አቅም ያላቸውን ግለሰቦች ከትምህርት ዝግጅታቸው ጋር ለማጣጣም ሙከራ ተደርጓል።
👉 የተማረ ግን የማይፈጽም ከሆነ አሁን ለምናስበው ጉዳይ የምንፈልገውን ውጤት ስለማያመጣ የተማረ፣ የመፈጸም ብቃት፣ የመከታተል ብቃት እና ዲሲፕሊን ያለው መሆኑን አብሮ ለማየት ተሞክሯል።
👉 ሁለተኛው የሥራ ልምድ ነው፤ በተሰማሩበት የሥራ መስክ ውጤት በማስመዝገብ እቅዳቸውን በማሳካት የተሻለ አፈጻጸም ያላቸውን ሰዎች እንዲሁ ለማየት ጥረት ተደርጓል።
👉 በተጨማሪም አሁን የምንጀምረው ዓመት እና የሚቀጥሉ 5 ዓመታት ብዙ መሮጥ ብዙ መፍጋት የሚጠይቅ ዘመን ስለሆነ ያን ሩጫ ለመሮጥ የሚያስችል ብቃት ያላቸውን ሰዎች ከግምት ለማስገባት ተሞክሯል።
👉 ከሁሉ ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ በብዙ ችግር በብዙ መከራ መንግሥት የማጽናት፣ መንግሥት የማስቀጠል፣ የመንግሥት ቁመናን የማሳደግ ፍላጎቱን በምርጫው 54 ሚሊየን ዜጎች በሚያስደምም ሁኔታ ከፍተኛ አደራ ጥለውብናል፤ ያን አደራ ለመሸከም የሚያስችል ትከሻ ያላቸው ሰዎች ያስፈልጋሉ።
👉 ህዝብ አብዝቶ የሚጠይቀውን አገልግሎት ለመስጠት ማገልገል መታደል ነው፣ ጸጋ ነው ብለው የሚያምኑ እንዲሆኑ ጥረት ተደርጓል።
👉 ኢትዮጵያ እስከ 2050 የሚዘልቅ የመደመር ግራንድ ስትራቴጂ አዘጋጅታለች።
👉 ይህን ግራንድ ስትራቴጂ በቅጡ የተረዱ በዚህ ግራንድ ስትራቴጂ ውስጥ የተቀመጡ ዐበይት ነጥቦችን ከነ ዝርዝር እሳቤያቸው የተገነዘቡ በተለይ 2 ነገር ላይ አበክረው እንደሚሰሩ በነበረን የስልጠና ሂደት ብቃታቸውን ያረጋገጡ ግለሰቦች ላይ ለማተኮር ተሞክሯል።
👉 አንደኛው የዜጎች ጥቅም ነው። የኢትዮጵያ እድገት፣ የኢትዮጵያ ለውጥ፣ የኢትዮጵያ መሻሻል እያንዳንዱን ዜጋ የማይነካ ከሆነ ዋጋ የለውም።
👉 ዜጎችን የሚነካ እድገት ለማድረግ በሂደት እና በሥራ ውጤት (አውትፑት) ብቻ የሚረኩ ሳይሆን፤ በፋይዳ (አውትካም) ደረጃ የሚያስቡ እና ተጽዕኖውን (ኢምፓክት) የሚለኩ ግለሰቦች እንዲሆኑ ጥረት ተደርጓል።
👉 ይህ እንዳለ ሆኖ በተቻለ መጠን የብሔር ስብጥር፣ የጾታ ስብጥር፣ የእምነት ስብጥር ለመጠበቅ ጥረት ተደርጓል።
👉 ብቃት ልምድ ከወስድን በኋላ ጾታን፣ እምነትን፣ ብሄርን ታሳቢ ካላደረግን አሁን ያለውን ህብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያ ማንጸባረቅ ስለማያስችል እሱንም በተቻለ መጠን ከግምት ያስገባ እንዲሆን ጥረት ተደርጓል።
👉 ሲጠቀለል ዛሬ የማቀርባቸው የካቢኔ የዕጩ አባላት ከወትሮ በተለየ መንገድ ባለዕዳ፣ ከፍተኛ አደራ የተጣለባቸው ዛሬ መሾም ሸክም መሆኑን እንዲገነዘቡ በዚሁ አጋጣሚ ማሳሰብ እፈልጋለው።
👉 ሹመት የምንዝናናበት ሳይሆን የምንፈጋበት፣ የምንሰራበት ኢትዮጵያን ለማጽናት፣ ኢትዮጵያን ለማበልጸግ ኢትዮጵያን ወደ ስልጣኔ ጉዞ ለማስኬድ ከፍተኛ ጥረት የሚደረግበት የሥራ መስክ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል።
👉 ብዙ ምቾት ብዙ እንቅልፍ ብዙ ድሎት ያለው ጉዳይ ሳይሆን ብዙ ኃላፊነትና ድካም ያለው ጉዳይ መሆኑን እያንዳንዱ ዕጩ የካቢኔ አባላት ከወዲው እንዲገነዘቡ የምክር ቤት አባላትም ይሄንን ጉዳይ ታሳቢ አድርገን ለመሥራት ጥረት እንዳደረግን ከግምት እንዲያስገቡ አስቀድሜ አሳስባለሁ።
#የመደመር_መንግሥት
በሶስና አለማየሁ