Fana: At a Speed of Life!

በትምህርት ዘርፉ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎችን ዳር ለማድረስ በቁርጠኝነት ይሰራል – ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በትምህርት ዘርፉ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎችን ዳር ለማድረስ በከፍተኛ ትኩረት ይሰራል አሉ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)።

ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በድጋሚ የትምህርት ሚኒስትር ሆነው በዛሬው ዕለት ተሹመዋል።

ሚኒስትሩ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በነበራቸው ቆይታ÷ በትምህርት ዘርፉ እየተካሄደ ያለው የሪፎርም ሥራ ሙሉ ለሙሉ አለመጠናቀቁን ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፍላጎት የትምህርት ዘርፉ ሪፎርም በተጀመረው መልኩ ዳር እንዲደርስ መሆኑን ጠቁመዋል።

ስለሆነም በዘርፉ እየተካሄደ የሚገኘውን ሪፎርም በስኬት ለማጠናቀቅ ከበፊቱ በተጠናከረ ሁኔታ በቁርጠኝነት ይሰራል ነው ያሉት።

በዚህም መሠረት የትምህርት ሥርዓቱን በመሠረታዊነት መቀየርና የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ የቀጣይ ዋና ሥራችን ይሆናል ብለዋል።

የመንግሥት ጉዳይ የሀገር ጉዳይ ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ደግሞ የሁሉም ፖለቲከኛ ቀዳሚ ጉዳይ ሊሆን እንደሚገባ አስረድተዋል።

የሚመጡ ችግሮችን ለመቋቋም በአንድነት መቆም እንደሚያስፈልግ ጠቁመው÷ የተጀመረው ሀገርን ማዕከል ያደረገ የፖለቲካ ሥርዓት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያን ማዕከል ማድረግና የሀገርን ጥቅም ለምንም ጉዳይ አሳልፎ አለመስጠት እንዲሁም የሚነሱ ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት ልምድን ማዳበር እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።

#የመደመር_መንግሥት

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.