Fana: At a Speed of Life!

የሠንደቅ ዓላማ ቀን ዜጎች የጋራ እሴቶቻቸውን የሚያጠናክሩበት ታላቅ ሀገራዊ ሁነት ነው – ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ)የሠንደቅ ዓላማ ቀን ዜጎች የጋራ እሴቶቻቸውን የሚያጠናክሩበት ታላቅ ሀገራዊ ሁነት ነው አሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ፡፡

19ኛው የሠንደቅ ዓላማ ቀን በጋምቤላ ከተማ በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች ተከብሯል፡፡

ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና አንድነት ለማስጠበቅ የተከፈለው ከፍተኛ መስዋዕትነት መግለጫ ከመሆኑም በላይ፤ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም የነጻነት ምልክት ሆኖ ያገለገለ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን በብዝሃነታቸው ውስጥ ባለው በደም የተሳሰረ አንድነትና ወንድማማችነት የውስጥና የውጭ ጠላቶችን ጥቃት በመመከት ሀገራዊ ሉዓላዊነትን አስከብረው መኖራቸውን አስታውሰዋል።

የክልሉ ህዝብ ሀገርን በመጠበቅ ላይ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዲያደርግ፣ ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ሰላም እንዲጠብቅ እንዲሁም ለክልሉና ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልጽግና መረጋገጥ በጋራ መቆም እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ዜጎች ለሀገር ምልክትና ሉዓላዊነት ያላቸውን ክብርና ፍቅር የሚገልጹበት እንዲሁም የጋራ እሴቶቻቸውን የሚያጠናክሩበት ታላቅ ሀገራዊ ሁነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያውያንን የመስዋዕትነት ታሪክና የሉዓላዊነት ማረጋገጫ ምልክት የሆነውን ይህን ዕለት በድምቀት ማክበር እና መዘከር ተገቢ ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡

ቀኑ የኢትዮጵያውያንን የአንድነት፣ የነጻነት እና የሉዓላዊነት ክብር የሚያንጸባርቅ ትልቅ በዓል ነው ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.