Fana: At a Speed of Life!

ከኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርጥ የሚባል ተሞክሮ አግኝተናል – የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዚዳንት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በቀዳማይ ልጅነት ልማት ዘርፍ እያከናወነች ካለችው ተግባር በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርጥ የሚባል ተሞክሮ አግኝተናል አሉ የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዚዳንት ካሺም ሺቲማ።

በምክትል ፕሬዚዳንቱ የተመራ ከፍተኛ ልዑክ “በሥርዓተ ምግብ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት” በሚል መሪ ሐሳብ ለሦስት ቀናት በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አድርገዋል።

ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ በሚዲያ ረዳታቸው በኩል በሰጡት መግለጫ÷ ከኢትዮጵያ የተገኙት ተግባራዊ ትምህርቶች በናይጄሪያ የተጀመረውን የሥርዓተ ምግብ ፕሮግራም ወደ ተጨባጭ ውጤት ለማሸጋገር እንደሚያግዙ ጠቁመዋል።

በተለይም ከኢትዮጵያ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም የተገኘው ልምድ በናይጄሪያ የሥርዓተ ምግብ ኢኒሼቲቭን ለመተግበር አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል።

በሦስተኛው የጉብኝታቸው ቀን በአዲስ አበባ በመገኘት የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራሙን አፈጻጸም የተመለከቱት ምክትል ፕሬዚዳንቱና ልዑካቸው ከጉብኝቱ ያገኙት ልምድ በሀገራቸው የጀመሩትን ተነሳሽነት ወደ ተግባራዊ እርምጃ ለማሸጋገር እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ የሚተገበረው የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም በቅድመ መደበኛ ትምህርት፣ በጤና እንክብካቤ፣ በሕፃናት ማቆያ እና በወላጆች ሥልጠና ላይ ያተኮረ መሆኑም በመግለጫው ተነስቷል።

ፕሮግራሙ ለናይጄሪያው ልዑክ ጠቃሚ ተግባራዊ ትምህርቶችን ያስገኘ መሆኑን የናይጄሪያው ጋዜጣ ዚስ ዴይ ዘግቧል።

#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.