የዲሲፕሊን ልዕልና ባለቤት፦ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአንድ ሀገር ህልውና፣ ሉዓላዊነት እና የህዝብ ደህንነትን ማስከበር ሂደት ውስጥ የጠንካራ የዲሲፕሊን ባለቤት የሆነ ሠራዊት ሚና ምትክ የለሽ ነው።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከረጅም ዘመናት የውጊያና ሀገር የማስከበር ታሪኩ ባሻገር፣ በልዩ ወታደራዊ ዲሲፕሊኑ እና ለህዝብ ባለው ታማኝነት የሚታወቅ የሀገር አለኝታ እና ጋሻ ነው።
ይህ ታላቅ ሠራዊት የሚታወቅበት ከፍተኛ ዲሲፕሊን በድንገት የተገኘ ወይም በአንድ ጀንበር የመጣ አይደለም፤ ይልቁንም በጠንካራ የትምህርትና የስልጠና ተቋማት እንዲሁም በሀገራዊ እሴቶች ላይ የተገነባ እንጂ።
የዕዝ ሰንሰለቱን ጠብቆ የመንቀሳቀስ ልምዱ፣ ለሕገ መንግሥታዊ ተቋማት የሚሰጠው ሙሉ ታዛዥነት እና ከህዝብ ጋር ያለው ጥብቅ ቁርኝት የዲሲፕሊኑ ዋነኛ መገለጫዎች ናቸው።
ሠራዊቱ ሀገርን ከውጭ ላኪዎች እና ከውስጥ ተላላኪዎች ከመጠበቅ ባለፈ ብዙ ሀገራዊ ተግባራትን ያከናውናል፡፡
ሉዓላዊነትን ማስከበር፡ የሀገርን ዳር ድንበር እና የአየር ክልል ከማንኛውም የውጭ ትንኮሳ በፅናት መጠበቅ፣ ሀገራዊ ልማትና ድጋፍ ማድረግ፣ በጎርፍ፣ በድርቅና በሌሎች ተፈጥሮአዊ አደጋዎች ወቅት ህዝብን የመታደግና መልሶ የማቋቋም ሥራዎችን ማከናወን መገለጫዎቹ ናቸው።
ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ሰላምን ለማስጠበቅ በተባበሩት መንግሥታት እና በአፍሪካ ሕብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የላቀ አፈፃፀም ማሳየት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዋና ባህሪው ነው፡፡
ይህ ባህሪ የሚመጣው ታዲያ እንዲሁ አይደለም የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማዘመን የዓለምን ወታደራዊ ልምዶች ከሀገር ባህል እና እሴት ጋር አጣጥሞ በማየት በዲሲፕሊን የታነፀ ሠራዊት ማፍራትን ይጠይቃል፡፡
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ታዲያ በዚህ የሚታማ አይደለም ከራሱ አልፎ ለአፍሪካ እና ለጎረቤት ሀገራት ምሳሌ መሆን የሚችል ነው፡፡
ወታደራዊ ዲሲፕሊን ማለት የመሳሪያ ብቃት ብቻ ሳይሆን፣ የህዝብን አደራ በክብር የመሸከም እና ለሕገ መንግስታዊ ስርዓት የመገዛት ጥበብ ነው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ደግሞ ለዚህ ምሳሌ ነው፡፡
ሠራዊቱ በከፍተኛ ዲሲፕሊን የታነፀ፣ ለህዝብና ለሀገር ፍቅር የታመነ፣ እንዲሁም የሀገርን ሉዓላዊነትና የህዝብን ሰላም ለማስከበር በየዕለቱ መስዋዕትነት እየከፈለ ያለ የሀገር አለኝታ ነው።
ይህንን ሥነ ምግባሩንና ሙያዊ ብቃቱን አጠናክሮ በማስቀጠል ለቀጣናው ሰላም እና ለሀገራዊ ዕድገት የጎላ ሚና መጫወቱን ቀጥሏል።
በእመቤት ሲሳይ