የፓን-አፍሪካኒዝም ቀለማት፤ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በዘመናት ታሪካዊ ለውጦች ውስጥ ሉዓላዊነቷን በማስጠበቅ የምትታወቀው ታላቋ ሀገር ኢትዮጵያ ብሔራዊ ሠንደቅ ዓላማዋ የህዝቦቿ የጋራ ማንነት መገለጫ ነው፡፡
በአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት መሃል ላይ ጎልቶ በሚታይ ኮከብ የተወከለው የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ የሀገሪቱን ልምላሜ፣ ተስፋ፣ ጀግንነት እንዲሁም ብዝሃነት ይገልጻል፡፡
የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ የጋራ ታሪክን እና ርዕይን የሚያመላክት ብዝሃነትን ከአንድነት ጋር ያጣጣመ የብሔራዊ ክብር እና ተስፋ ምልክት ሆኖ ያገለግላል።
ቀደምት አባቶች ለዘመናት ነጻ ሀገርን አቆይተው፤ ለዓለም የነጻነት ታጋዮች መነሳሳት የሆነውን የክብር ውርስ እንደማስረከባቸው የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ከትውልድ ትውልድ በልጆቿ ቆራጥነት እና ታላቅ ፍቅር የጸናችውን ሀገር ታሪክ ይዘክራል።
ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች እጅ ለእጅ ተያይዘው ሀገራቸውን ለመከላከል የወደቁትን አርበኞች መስዋዕትነት በማሰብ በልዩነት ውስጥ የሚታየውን ውበት ለጋራ ዕጣ ፈንታ መወሰኛ ሃይልነት መጠቀም የሚያስችላቸውን ጥበብ በጉልህ ያመላክታል፡፡
የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ በዓለም አቀፍ ታሪክ ውስጥም ትልቅ ቦታ አለው።
ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ዘመን የጣሊያን ወራሪን በዓድዋ ጦርነት ድል በማድረግ እና የጣሊያንን ጥረት መና በማስቀረት ከአውሮፓ ቁጥጥር ውጭ መቆየት ችላለች።
በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ተላቅቀው ነጻነታቸውን ሲያውጁ ቅኝ ሳትገዛ ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ የኖረችው የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ የፓን-አፍሪካኒዝም ቀለማት በማለት የአፍሪካ ነጻነት እና የጸረ-ቅኝ ግዛት ተምሳሌት ሆና የቆየችበትን ታሪካዊ ክብር ገልጸዋል፡፡
የብዙ የፓን-አፍሪካ ድርጅቶች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቀለማት መቀበልም የዚህ ውጤት ነው።
የነፍስ ዋጋ ተከፍሎላት የጸናችን ሀገር የዘመኑ ትውልድ እርስ በእርስ በመደጋገፍ፣ የሰላም ድልድዮችን በመገንባት እና ለተሻለች ሀገር በትጋት መስራት የሀገር ፍቅርን በተግባር መግለጽ ይኖርበታል፡፡
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በምሕረት ደምሴ