የሴቶችን የመሬት ባለቤትነት ይበልጥ ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው – የግብርና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሴቶችን የመሬት ባለቤትነት በይበልጥ ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር)።
የዓለም የአርሶ እና አርብቶ አደሮች ቀን “ሴት አርሶ እና አርብቶ አደሮችን እናብቃ፤ የምግብ ዋስትናችንን እናረጋግጥ፤ የበለጸገች ኢትዮጵያን እንገንባ” በሚል መሪ ሃሳብ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተከበረ ነው።
ዕለቱ በግብርና ልማት የምግብ ዋስትናን እና የገጠር ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማረጋገጥ በሚከናወኑ ተግባራት ሴት አርሶ እና አርብቶ አደሮችን ለማበረታታትና ለሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እውቅና ለመስጠት ያለመ ነው።
በመድረኩ ላይ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) እንዲሁም የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሄለን ደበበን ጨምሮ ሴት አርሶና አርብቶ አደሮች ተገኝተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተጓዘች ባለችበት መንገድ የሴቶች ሚና ከፍተኛ ነው።
በተለይም ከቤተሰብ ፍጆታ አልፈው ምርትን ለማህበረሰቡ እያቀረቡ ውጤታማ ስራዎችን እየከወኑ እንደሚገኙ ገልጸው፤ ሆኖም የብድር አቅርቦት፣ የአየር ንብረትን የሚቋቋም ቴክኖሎጂና ከመሬት ባለቤትነት አንጻር ችግሮች እንደሚስተዋሉ አብራርተዋል።
እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ መንግሥት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በተለይም የሴቶችን የመሬት ባለቤትነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
ወደ ገጠሩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የፋይናንስ ተደራሽነት ለማስፋት በትኩረት እንደሚሰራም ነው የገለጹት፡፡
በፌቨን ቢሻው