የመደመር መንግሥት ስንፍናን እና ልግመኝነትን አይታገስም – የትምጌታ አስራት (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር መንግሥት ስንፍናን እና ልግመኝነትን አይታገስም አሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር)፡፡
በመደመር መንግሥት ህብረተሰብ አቀፍ የምክክር መድረክ በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ ተካሂዷል፡፡
የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የህዝቡን ፍላጎት ማዳመጥ፣ የህዝቡን ችግር መፍታት፣ ብልሹ አሰራር እና ሌብነትን አጥብቀን እንታገላለን፡፡
ኢትዮጵያ በተትረፈረፈ ሀብት ላይ ያለች ነገር ግን ያላትን ሀብት ያልተጠቀመች ሀገር መሆኗን አንስተው፤ ጸጋዎቻችንን በመጠቀም የህዝቡን ኑሮ ማሻሻል ላይ በትኩረት እንሰራለን ብለዋል፡፡
እንደ ሀገር በሁሉም ዘርፍ ውጤት ለማስመዝገብ አልቀን አስበን እየሰራን ነው ያሉ ሲሆን፤ የሰው ሀይል፣ የገንዘብ እና የተቋም አቅማችንን በማደራጀት ወደሚፈለገው የእድገት ደረጃ እንሸጋገራለን ሲሉም ገልጸዋል።
ግንባታቸው የተጓተቱ የልማት ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ የመደመር መንግሥት ባህሪ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በስፋት በማምረት የህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ላይ ያተኩራል ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ያቀድነውን ለማሳካት የውስጥ አንድነታችንን መጠበቅና ትኩረታችንን ልማት ላይ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
ይህ ዘመን ኢትዮጵያ ትልቅ አስባ፣ ትልቅ የምትከውንበትና በእጥፍ የምታመርትበት ጊዜ ነው ያሉ ሲሆን፤ ያቀድነውን ለማሳካት የውስጥ አንድነታችንን መጠበቅና ትኩረታችንን ልማት ላይ ማድረግ ይጠበቅብናል ሲሉም አመልክተዋል፡፡