በቂ የኃይል አቅርቦት የሌላት ሀገር ፈጣንና ዘላቂ ዕድገት ማረጋገጥ አትችልም -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በቂ የኃይል አቅርቦት የሌላት ሀገር ፈጣንና ዘላቂ ዕድገት ማረጋገጥ አትችልም አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽንን በዛሬው ዕለት ጎብኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ እንደ ኢትዮጵያ ያለች ትልቅ ሀገር መሰል ከበድ ያሉና ረጅም ጊዜ የሚወስዱ ፕሮጀክቶችን ቀድማ መጀመርና መሰረት መጣል ነበረባት፡፡
ሆኖም ከጉባ ብስራቶች በኋላ የባለሙያዎች ቡድን ተዋቅሮ ሰፊ ጥናት ሲደረግ መቆየቱን ጠቁመው፤ ተቋሙ በሕግ እንዲቋቋም ተደርጎ አስፈላጊው የሰው ሀብት ተመድቦለት ወደ ሥራ መግባቱን አብራርተዋል።
ይህ ቴክኖሎጂ ከኃይል ምንጭነት ባሻገር ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጥቅምን እንደሚያመጣ አንስተው፤ በተለይም በጤናው ዘርፍ ለካንሰር ሕክምና ከፍተኛ ውጤታማነት ያለው በመሆኑ የሕክምና አገልግሎትን ለማዘመንና ለማስፋፋት የጎላ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
በግብርናው ዘርፍ ምርታማነትን በመጨመር ሀገሪቱ በምግብ ራስን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት የሚያፋጥን አጋዥ ቴክኖሎጂ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከፍተኛ ብቃት ያላቸውን የሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ለመፍጠር ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር የተሳሰረ ሰፊ ሥራ እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።
በቂ የኃይል አቅርቦት የሌላት ሀገር ፈጣንና ዘላቂ ዕድገትን ማረጋገጥ አትችልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ሀገራዊ የኃይል ፍላጎትን ለማሟላት አማራጮችን ማስፋፋትና ከንጹህ ምንጮች መካከል ደግሞ የኒውክሊየር ቴክኖሎጂን መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በመልካም ፈቃዱ