የመደመር መንግሥት አሸናፊ ሀሳብ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል – አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር መንግሥት የያዘው አሸናፊ ሀሳብ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል አሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ።
በኦሮሚያ ክልል የፓርቲና የመንግሥት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ መካሄድ ጀምሯል።
አቶ ሽመልስ አብዲሳ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ሕዝባችን በቁርጠኝነት በሚመራ የለውጥ መሪ ሲመራ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት እንደሚችል በተግባር አሳይቷል ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ማኅበረሰቡን መለወጥ የሚችል አስተሳሰብ በመተግበሩ ጥሩ የሥራ አፈጻጸም መመዝገቡን ገልጸዋል።
ያገኘነውን ዕድል በሁሉም መስክ በአግባቡ ተጠቅመን ወደ ተግባር ባለመቀየራችን እንደሚፈለገው ለመጓዝ ያልቻልንባቸው ሁኔታዎች አሉ ሲሉ ጠቁመዋል።
ሥራ አጥነት፣ በሚሰጡ አገልግሎቶች ላይ የሚታዩ ክፍተቶችና ሙስና በቀደሙት ዓመታት ማነቆ እንደነበሩ አስታውሰው፤ በቀጣይ ሕዝባችንን በኢኮኖሚና በዕውቀት ለማብቃት የያዝነውን ዓላማ ለማሳካት ብዙ ሥራ ይጠብቀናል ብለዋል።
በኦሮሞ ስም እንታገላለን የሚሉ አካላት የኦሮሞን ዓላማ በመካድ፣ ተቃራኒ አስተሳሰብ ካላቸው ኃይሎች ጋር በመሰለፍ ሕዝቡን ለመጉዳት እየሠሩ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ይህም ህዝብን የማዳከም ዓላማ እንዳለው ጠቁመዋል።
የተያዙ ዕቅዶችን ለማሳካት ያለውን አቅምና ብቃት በመለየት፣ የሚጎድሉትን ነገሮች በማሻሻልና ኃላፊነትን በመወጣት መሥራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
በየደረጃው ያሉ አስፈጻሚ አካላት በቁርጠኝነት እንዲሠሩ አቅጣጫ የሚያሳይ ጠንካራ አመራር መስጠት፣ የቤተሰብ ብልጽግናን ማረጋገጥና ሕዝቡን በኢኮኖሚ ለማብቃት በትጋት መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የክልሉን ገቢ አሰባሰብ በማጠናከር የአገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያሉ የሙስና ማነቆዎችን ማስወገድና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
የተጀመረው የባህል እድሳት ወደታሰበው ግብ እንዲደርስና የኦሮሞ ብሔራዊ ማንነትና ኩራት እንዲያድግ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አቶ ሽመልስ ገልጸዋል።
የተያዙ ዕቅዶችን ለማሳካት በቂ ዝግጅት ያለውና የበሰለ ውይይት ማድረግ፣ የታዩ ክፍተቶችን በግልጽ መለየትና በተግባር የሚተረጎም የሥራ አቅጣጫ መቀመጥ እንዳለበትም አመልክተዋል።
በአቤል ነዋይ