ሀረር በፍቅርና በመቻቻል የሚኖሩባት ከተማ ናት ¬- አቶ ኦርዲን በድሪ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀረር በሰላም፣ በፍቅርና በመቻቻል የሚኖሩባት ከተማ ናት አሉ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በኢትዮጵያ የሮማኒያ አምባሳደር ጁሊያ ፓታኪን ጋር ተወያይተዋል።
በዚህ ወቅት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ በክልሉ ያለውን የቱሪዝም ሀብት ለማልማት የተሰጠውን ትኩረት እንዲሁም እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል።
ሀረር ከተማ የጁገል ቅርስን ጨምሮ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገቡ ዓለም አቀፍ ቅርሶች መገኛ መሆኗን እብራርተዋል።
ከተማዋ የተለያዩ ባህል እና እምነት ያላቸው ህዝቦች በሰላም፣ በፍቅርና በመቻቻል የሚኖሩባት መሆኗን አስረድተዋል፡፡
ሮማኒያ በትምህርት ዘርፎ እያደረገች ላለው ድጋፍም አመስግነዋል።
አምባሳደር ጁሊያ ፓታኪ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ እና ሮማኒያ ግንኙነት ዘመናትን ያስቆጠረ እና በመልካም ወዳጅነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ገልፀዋል።
በትምህርት ረገድ የቆየ ግንኙነት ያላቸው ኢትዮጵያና ሮማኒያ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አጋር መሆናቸውንም አስታውሰዋል።
በቀጣይ በቱሪዝም እና ማህበራዊ ልማት ስራዎች ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።
በውይይቱ መጨረሻም አምባሳደሯ ለአውአብዳል ኢንስቲትዩት የኢኮቴ ላብራቶሪ እና መሳሪያዎች ድጋፍ ማድረጋቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡