አዲስ ውበት ለአዲስ አበባ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ዘመናዊ ከተሞች የሚለኩት በስፋታቸው፣ በሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎቻቸው እና በመብራቶቻቸው ብቻ ሳይሆን ዘመናዊ መሰረተ ልማትን ከተፈጥሮ ጋር በማጣመር ለነዋሪዎች ምቹ አካባቢ በመፍጠራቸው ጭምር ነው፡፡
አዲስ አበባም በተፈጥሮ የተቸሯትን ሃብቶች አልምቶ መጠቀም የዘመናዊ ከተማነቷ መገለጫዎች ካደረገች ዋል አደር ብላለች፡፡
በመደመር መንግሥት ትኩረት ከተደረገባቸው መስኮች አንዱ በሆነው የከተሞች ልማት ፕሮጀክት ከተማዋ የወንዞቿን ዳርቻ በማልማት ወደ አዲስ የከተማ ልማት ገጽታ እየተሸጋገረች ትገኛለች።
በቅርብ የተመረቀው ቀጨኔን መነሻው አድርጎ ባምቢስ የሚዘልቀው የወንዝ ዳርቻ ልማትም ቀደም ሲል በብክለትና በተፈጥሮ መራቆት የተጎዱ አካባቢዎችን ወደ ውብ እና አረንጓዴ የመዝናኛ ስፍራነት ቀይሯቸዋል፡፡
አዲስ አበባ የወንዞቿን ዳርቻ በማልማት የከተማዋን ውበት ብቻ ሳይሆን፤ ለነዋሪዎች ምቾት የሚሰጥ፣ ከተፈጥሮ ጋር የተጣጣመና ለማህበረሰቡ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚያግዝ የከተማ ሕይወት እየገነባች ነው።
ርዕይዋም ወንዞችን ከብክለትና ከተፈጥሮ መራቆት በማውጣት ለአካባቢ ጥበቃ ተስማሚ፣ ለቱሪዝም፣ ለንግድ እና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የሚያግዙ ማዕከላት ማድረግ ነው።
ይህም የከተማዋን ውበት ከማሳደግ ባለፈ የመዝናኛ ስፍራ፣ የሥራ ዕድል እና የገቢ ምንጭ በመሆን ለከተሜነት ህይወት መሠረት ሆኗል፡፡
ይህ ለውጥ አዲስ አበባ ያላትን የቱሪዝምና የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ለማጠናከር፣ የከተማዋን ገጽታ ለማሻሻልና የነዋሪዎችን የኑሮ ጥራት ለማሳደግ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡
ይህም የከተማዋን ወንዞች ከየተፈጥሮ መልክዓ ምድርነት በማሻገር የነዋሪዎች ማህበራዊ ሕይወትና ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አካል ማድረግ አስችሏል።
እነዚህ ስፍራዎች ለነዋሪዎች እንዲሁም ለጎብኚዎች ምቹ ማረፊያ እና መዝናኛ ከመሆናቸው ባሻገር ለወጣቶች የሥራና የፈጠራ ዕድሎችን አስፍቷል።
ለአካባቢው ነጋዴዎችና አገልግሎት ሰጪዎችም አዳዲስ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች እንዲፈጠሩ መንገድ ከፍቷል።
የወንዞች ዳርቻን በአግባቡ ማልማት የተፈጥሮ ሀብትን ለመጠበቅ፣ የከተማዋን አረንጓዴነት ለማሳደግና ብክለትን ለመቀነስ የሚኖረው ሚና የጎላ ነው፡፡ የነዋሪዎችን የኑሮ ሁኔታ ከማሻሻል ባለፈ ለከተማዋ ዘላቂ እድገትም ጠንካራ መሠረት ይሆናል።
የወንዝ ዳርቻዎች የከተማዋን ውበት አጉልቶ በማሳየት የቱሪዝም መስህብነቷን በማጠናከር አህጉራዊ የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችውን አዲስ አበባን ገጽታ ይበልጥ ለማጎልበት የሚያግዙ እምቅ ሀብቶች ናቸው።
የተገነቡ መንገዶችና የለሙ መልክዓ ምድሮች እንዲሁም የወንዝ ዳርቻዎች ዘላቂነት በአካባቢው ማህበረሰብ እንዲሁም በጎብኚዎች እንክብካቤ እና የአጠቃቀም ሥነ ሥርዓት ይወሰናል፡፡
በምሕረት ደምሴ