በሩብ ዓመቱ ከ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ አረቦን ተሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በሩብ ዓመቱ ከ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ አረቦን ተሰብስቧል አለ የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ።
ፈንዱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸሙን አስመልክቶ ለፋና ዲጂታል በላከው መግለጫ÷ አፈጻጸሙ ከዕቅዱ ጋር ሲነጻጸር የ100 በመቶ ስኬት የተመዘገበበት መሆኑን አስታውቋል።
ይህ አፈጻጸም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ25 ነጥብ 48 በመቶ ብልጫ እንዳለውም ጠቁሟል።
ይህ ውጤት የአባል ፋይናንስ ተቋማት የተቀማጭ ገንዘብ መጠን በመጨመሩ ምክንያት መሆኑን በማንሳት ፈንዱ ሥራውን በይፋ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ከአባል የፋይናንስ ተቋማት የሰበሰበው ጠቅላላ አረቦን 26 ነጥብ 03 ቢሊየን ብር መድረሱን ገልጿል።
በሌላ በኩል ፈንዱ የገንዘብ አቅሙን ለማሳደግና ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት የተሰበሰበውን አረቦን በመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድ እና በሙዳራባህ የጊዜ ገደብ የቁጠባ ሂሳብ ላይ ኢንቨስት እያደረገ እንደሚገኝ አመልክቷል።
በዚሁ መሠረት በሩብ ዓመቱ የፈንዱ ጠቅላላ የኢንቨስትመንት መጠን 27 ነጥብ 24 ቢሊየን ብር መድረሱን እና ፈንዱ ወደ ሥራ ከገባ ወዲህ ከኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው እስከ አሁን 4 ነጥብ 97 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን ጠቅሷል።