የተሟላ ዝግጁነት ያለው አመራር
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገር ሥልጣኔና ዘላቂ ብልጽግና የሚመጣው የኢኮኖሚ ዕድገትና ቁሳዊ ሀብቶችን በማዳበር ብቻ ሳይሆን እሴቶችን፣ የባህል ማንነትን እና የሞራል ጥንካሬን በመገንባት እንዲሁም ዕውቀትን ከማኅበራዊ ኃላፊነት ጋር በማቀናጀት ጭምር ነው።
ለዚህ የሥልጣኔ ግንባታ ሂደት በሁሉም ዘርፎች የተዘጋጀ፣ በእውቀትና በሥነ ምግባር የታነጸ እና የሀገርን ራዕይ ወደ ተግባር የሚቀይር አመራር ያስፈልጋል።
በሙያዊ ዕውቀት፣ በመንፈስ ብርታትና በተግባር የሚገለጥ ጥበብ የተሟላ አመራርን ብቁነት የሚያሳዩ መለያዎች ሲሆኑ፤ በተለይም ለሀገር ፍቅር፣ ለሕዝብ ጥቅምና ለተሰጠው ኃላፊነት ቁርጠኛ መሆን የአመራር ስብዕና ዋነኛ መገለጫዎች ናቸው።
በዚህ ረገድ ወታደራዊ ሳይንስና ሥልጠና ከጦርነት ዝግጅት በላይ የሆኑ ልምድና ተሞክሮ መቅሰሚያዎች እንደመሆናቸው መጠን የዲሲፕሊን፣ የጽናት፣ ራስን የመግዛት፣ የቡድን ሥራና የኃላፊነት ባህልን ያዳብራሉ።
የተሰጠን ግዳጅ በብቃት መፈጸም፣ በጋራ ዓላማ ዙሪያ መናበብ፣ በተዋረድ መሥራት፣ ተጠያቂነት እና ለማንኛውም ዓይነት ፈተና በቅድሚያ መዘጋጀት ከወታደራዊ ልምድ ሊወሰዱ የሚችሉ ጠቃሚ እሴቶች ናቸው።
እነዚህን እሴቶች ወደ አመራር ሥርዓት በማምጣት የመደመር መንግሥት አመራሮች በሁርሶ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ማዕከል ሥልጠና ወስደዋል። ሥልጠናው ከወታደራዊ ሳይንስና ሕይወት የሚገኙ ዕውቀቶችን፣ ክህሎቶችንና የአመራር ልምዶችን በመቅሰም ሀገራዊ ግቦችን የማስፈጸም አቅም ለማጠናከር ያለመ ነው።
የሀገራዊ ራዕይን ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመቀየር የተቋማት ቅንጅት፣ የሀብት አጠቃቀም፣ የሕዝብ ተሳትፎና የአፈጻጸም ብቃት ወሳኝ ናቸው።
በመሆኑም ሥልጠናው ከታች እስከ ላይ ያሉ መዋቅሮችን በአንድ ዓላማ ዙሪያ ማስተባበር፣ የሰው ኃይልንና የሀገር ሀብትን በተገቢው መንገድ መጠቀም፣ ሕዝብን ለጋራ ዓላማ ማነሳሳትና የተገቡ ቃል ኪዳኖችን በተግባር መፈጸም ላይ ትኩረት አድርጓል።
ከዚህ ባሻገር ጠንካራና ተቋማዊ መሠረት ያለው ሀገር መገንባት፣ የሀገርን ደኅንነት ማረጋገጥ፣ ተተኪ ትውልድን ማፍራትና ሀገራዊ ጥቅምን ማስቀደም እንዲሁም የህዝብ አደራን በኃላፊነት መጠበቅ የሚያስችል የአመራር ቁመናን የሚያጎለብቱ ናቸው።
ለእነዚህ ግቦች መሳካት ሕዝብንና ተቋማትን በጋራ ማሳተፍ አስፈላጊ ነው። በወታደራዊና በሲቪል አመራር መካከል የሥራ ባህሪ ልዩነት ቢኖርም፣ ሁለቱም የጋራ ዓላማን በውጤታማነት የማሳካት ግብ አላቸው።
ወታደራዊ ሥራ ዒላማን ማሳካትን ሲጠይቅ፣ ሲቪል አመራር ደግሞ የሕዝብን ኑሮ ማሻሻልና ሰፊ ሀገራዊ ዓላማዎችን ማሳካትን ይጠይቃል። ከሁለቱ የሥራ ልምዶች የሚገኙ ጠቃሚ እሴቶችን ማቀናጀት የአመራርን ውጤታማነት ለማጎልበት ይረዳል።
ለሀገራዊ ዘላቂ ሥልጣኔ የሚደረገው ጉዞ ትልቅ ራዕይን ከተግባራዊ አቅም፣ የአመራር ዝግጁነትን ከሕዝብ ተሳትፎ፣ ዲሲፕሊንን ከተጠያቂነት ጋር ማጣመርን ይጠይቃል።
ሁለንተናዊ ብልጽግና ሁለንተናዊ ዝግጁነትን እንዲሁም ሀገራዊ ዓላማን በዕውቀት፣ በዲሲፕሊን፣ በቁርጠኝነትና በተግባር የተደገፈ አመራርን መንገንባት ነው።
የሁርሶው የአመራሮች ሥልጠናም ይህንን ግንዛቤ በማጠናከር የተነደፉ ሀገራዊ ርዕዮችን በብቃት የሚያሳካ፣ ምሉዕ ዝግጁነት ያለውና ለሕዝብና ለሀገር ጥቅም የሚቆም አመራር ለመገንባት ወሳኝ ነው።
በምሕረት ደምሴ