በሀረሪ ክልል ከ5 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት ወደ ሥራ ተገብቷል – ወ/ሮ ሮዛ ኡመር
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የመስኖ ልማትን ውጤታማ በማድረግ በክልሉ በዝናብ እጥረት የተከሰተውን የምርት መቀነስ ለማካካስ እንሰራለን አሉ የሀረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሮዛ ኡመር፡፡
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ የክልሉን የበጋ የመስኖ ልማት ሥራ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንዳሉት÷በክልሉ የውኃ አማራጮችን በመጠቀም ከ5 ሺህ 500 ሔክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት ወደ ሥራ ተገብቷል።
የበጋ መስኖ ልማትን ውጤታማ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው ይህን ሥራ ለማሳካት የግብርና ግብዓት በወቅቱ ለአርሶ አደሩ እንዲደርሱ እተደረገ ነው ብለዋል።
የመስኖ ልማትን ውጤታማ በማድረግ በክልሉ በዝናብ እጥረት የተከሰተውን የምርት መቀነስ ለማካካስ እንደሚሰራም አመልክተዋል።
የበጋ መስኖ ልማቱን የማሳደግ ዋና ዓላማው ምርታማነትን የማሳደግ፣ ገበያን የማረጋጋት እና አርሶ አደሩን ከተረጂነት ማውጣት ነው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል።
ከዚህ በተጨማሪ ለአርሶ አደሩም ስልጠና መሰጠቱን የገለጹት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ ለተግባራዊነቱ የግብዓት አቅርቦት፣ የክህሎት ሥልጠና እና የባለሙያ የቴክኒክ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።