የሳይበር ሉዓላዊነት የዲጅታል ቴክኖሎጂ አቅም ማሳያ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በዲጂታል ምህዳር እና በሳይበር ሉዓላዊነት ዙሪያ ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች የሀገሪቱን ብሔራዊ ደህንነት፣ የዜጎችን ተጠቃሚነት እና የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሠረት ጥለዋል።
የሳይበር ሉዓላዊነት እና የሳይበር ደህንነትን ማስጠበቅ ከሀገር ሉዓላዊነት፣ ከብሔራዊ ደህንነት እና ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ጥብቅ ትስስር አለው።
በአሁኑ የዲጂታል ዘመን የሳይበር ምህዳር ከመረጃ ልውውጥ ባለፈ የሀገራት የጂኦፖለቲካዊ ሽኩቻ እና የስትራቴጂካዊ የበላይነት መፋለሚያ መድረክ እየሆነ መጥቷል።
የመደመር መንግሥት ይህንን ነባራዊ ሁኔታ ተገንዝቦ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) አማካኝነት የዲጂታል ምህዳርን ከሳይበር ስጋት የመጠበቅ እና የ”ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030″ ራዕይን እውን የማድረግ ስራዎችን በስፋት እያከናወነ ይገኛል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ እና መሠረተ ልማት ለማሳደግ በተደረገው ጥረት የኢንተርኔት ተጠቃሚነት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲስፋፋ፣ የቴሌኮም ዘርፉ ለውድድር ክፍት እንዲሆን እና የመንግሥት አገልግሎቶች በዲጂታል መንገድ እንዲቀላጠፉ ተደርጓል።
የሀገር በቀል ቴክኖሎጂ እና የሳይበር ደህንነት አቅም ግንባታ ዘርፍ የሳይበር ጥቃቶችን የመከላከል እና የራስን የቴክኖሎጂ አቅም የማሳደግ ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን ይህ ስኬት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ትልቅ አርዓያ እና ምሳሌ ሆኗል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችን በሀገር በቀል አቅም በማልማት እና የሳይበር ደህንነት ባለሙያዎችን በማፍራት የዲጂታል ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ ጥረት እያደረገች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነትን የፖሊሲ ማሻሻያ ያደረገች ሲሆን በየጊዜው ከሚቀያየሩት የሳይበር ስጋቶች እና ዓለም አቀፍ አሰራሮች ጋር ለመጣጣም አጠቃላይ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲዋን አሻሽላ ሥራ ላይ አውላለች።
በተመሳሳይ የመረጃ እና ግብይት ሕጎች የግል መረጃ ጥበቃ፣ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት እና ፊርማ እንዲሁም የቴሌኮም ማጭበርበር መከላከያ ሕጎችን አውጥታ እየተገበረች ነው።
ሀገር በቀል የሶፍትዌር ልማት፣ የቴክኖሎጂ ፍተሻ፣ የዲጂታል ፎረንሲክ ላቦራቶሪ እንዲሁም የሳይበር ድንገተኛ አደጋ ምላሽ ቡድን መቋቋሙ ኢትዮጵያ ለዘርፉ የሰጠችውን ትኩረት ያሳያል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ውስጥ የተቀመጡትን የዲጂታል ሉዓላዊነት እና የማይበገር የሳይበር ደህንነት አቅም የመገንባት ግቦች ለማሳካት ያከናወነቻቸው ተግባራት ስኬት እያስመዘገቡ ይገኛሉ፡፡
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በሚኪያስ አየለ