አረንጓዴ ኢኮኖሚ፤ ለትውልድ የሚሻገር የብልጽግና መሠረት
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረ ባለበት በዚህ ዘመን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ማጣመር ምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ሆኗል።
የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም፣ የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ መጠቀምና ለትውልድ የሚሻገር ኢኮኖሚያዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ የዘመኑ ዋነኛ የልማት ጥያቄዎች ናቸው።
የአየር ንብረት ለውጥ ከአካባቢ ጥበቃ ጉዳይነት አልፎ የምግብ ዋስትናን፣ የውሃ ሀብትን፣ የኃይል አቅርቦትን፣ የኢንዱስትሪ ምርታማነትንና አጠቃላይ የኢኮኖሚ መረጋጋትን የሚፈትን ዓለም አቀፍ እውነታ ሆኗል።
ድርቅ፣ የጎርፍ አደጋ፣ የሙቀት መጨመርና የዝናብ ወቅቶች መዛባት በተለይም በግብርና ላይ ጥገኛ በሆኑ ኢኮኖሚዎች ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩ ይገኛሉ።
አረንጓዴ ኢኮኖሚ ማለት የኢኮኖሚ ዕድገትን ሳያቋርጡ የተፈጥሮ ሀብትን በቁጠባና በብቃት መጠቀም፣ የብክለት መጠንን መቀነስ፣ ታዳሽ የኃይል ምንጮችን ማስፋፋትና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የልማት መሠረት መገንባት ማለት ነው።
የዚህ አቀራረብ ዋነኛ ግብ የዛሬ ልማትን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን የነገውን ትውልድ የልማት ዕድል ሳያሳጣ የዛሬውን ፍላጎት ማሟላት ነው።
ኢትዮጵያም ይህንን እውነታ በመገንዘብ፤ የተፈጥሮ ጸጋዎቿን በዘላቂነት በመጠቀም ለትውልድ የሚሻገር አረንጓዴ የብልጽግና አድማስን በመቅረጽ እየተገበረች ይገኛል።
የኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ጉዞ መሠረቱ በሀገሪቱ እምቅ የታዳሽ ኃይል ሀብቶች ላይ የተገነባ ነው።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በሀገሪቱ የሚፈሰው ውሃ፣ የሚነፍሰው ነፋስ፣ የ13 ወር የፀሐይ ሀብት፣ የተፈጥሮ ጋዝ እምቅ አቅም የኢንዱስትሪና የኢኮኖሚ አቅጣጫ የሽግግር ማዕዘናት ናቸው።
የነዳጅ ጥገኝነትንና የከተሞችን የአየር ብክለት ለመቀነስ የትራንስፖርት ዘርፉን በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የማዘመን ሥራ በስፋት እየተተገበረ ነው።
ኢትዮጵያ በሶማሌ ክልል ካሉብ እና በሌሎች የኦጋዴን አካባቢዎች የሚገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ሀብት ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪና ለኃይል አማራጭነት ማዋል ጀምራለች።
በተጨማሪም ለወደፊት የኢንዱስትሪ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚኖረውን የሰላማዊ የኒውክሌር ኃይል ቴክኖሎጂ ለመጠቀም “የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኢነርጂ ኮሚሽን” ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱ የረጅም ጊዜ አርቆ አስተዋይነቷ ማሳያ ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የዛፍ ተከላ ብቻ ሳይሆን የተራቆቱ መሬቶችን መመለስ፣ የውሃ ሀብት ጥበቃን እና ድርቅን የሚቋቋም ዘመናዊ ግብርናን ያካተተ ሰፊ ሀገራዊ ዘመቻ ነው።
ከዚህ ጎን ለጎን በከተሞች ውስጥ በመስፋፋት ላይ ያሉት የአረንጓዴ ስፍራዎች ከተሞች የተፈጥሮ ሚዛናቸውን እያስጠበቁ ለነዋሪዎች አመቺ እየሆኑ እንዲመጡ በማስቻል ላይ ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስኬት በተፈጥሮ መታከም፣ በዜጎች ኑሮ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በኢኮኖሚያዊ መረጋጋት ላይ እያመጡት ባለ ተጨባጭ ለውጥ እየታየ ይገኛል።
በመልካም ፈቃዱ