ደቡብ ኮሪያ ለሰው ሰራሽ አስተውሎት ልማት ከ15 ቢሊየን ዶላር በላይ መደበች
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ደቡብ ኮሪያ ለሰው ሰራሽ አስተውሎት ልማት 15 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር በጀት መደበች፡፡
የሰው ሰራሽ አስተውሎት ለዓለም የወደፊት ኢኮኖሚያዊ የበላይነት ዋና መሰረት እየሆነ በመምጣቱን ተከትሎ በርካታ ሀገራት ለቀጣዩ ትውልድ ዲጂታል መሠረተ ልማት ከፍተኛ በጀት እየመደቡ ይገኛሉ።
ደቡብ ኮሪያም የመደበችው ይህ ከፍተኛ በጀት በሶስት ዋና ዋና የቴክኖሎጂ ሜጋ ፕሮጀክቶች ማለትም በከፍተኛ ሴሚኮንዳክተሮች፣ ፊዚካል አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እና በዘመናዊ የውሂብ ማዕከላት ልማት ላይ ለማዋል ማቀዷን ናይትድ ፕሬስ ኢንተርናሽናል ዘግቧል፡፡
ሀገራት በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ ከፍተኛ ፉክክር ውስጥ የገቡ ሲሆን፤ የሀገራት ፉክክር የቴክኖሎጂ አቅርቦት ሰንሰለቶቻቸውን፣ የኃይል ማከፋፈያዎቻቸውን እና የውሃ አቅርቦታቸውን በመጠበቅ በዓለም አቀፍ የዲጂታል ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል ያለመ ነው።
ይህ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ የሰው ሰራሽ አስተውሎት በሀገራት ዘንድ ቀዳሚ ብሔራዊ ትኩረት ተደርጎ መወሰዱን የሚያሳይ ነው።
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ አዳጊ እና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት በጠንካራ የሀገር ውስጥ አቅም ላይ የተመሰረተ መሆኑን እየተገነዘቡ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የዘርፉ ዕድገት ጋር አብሮ ለመራመድ እና በምስራቅ አፍሪካ የቴክኖሎጂ ማዕከል ለመሆን ስትራቴጂካዊ የዲጂታል ልማት ስራዎችን በማከናወን ላይ ትገኛለች።
ሙሉ ለሙሉ ትግበራው የተጠናቀቀው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ማዕቀፍ ውስጥ ሀገሪቱ በዘመናዊ የኮምፒዩቲንግ አቅም፣ በውሂብ መሠረተ ልማት እና በሰው ሃይል ልማት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ በመስራቷ በዘርፉ ከፍተኛ ስኬት ተመዝግቧል።
ሁለተኛው ምዕራፍ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂም እየተተገበረ ሲሆን የሀገሪቱን የዲጂታላይዜሽን ጥረት ከፍ ያደርገዋል፡፡
በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጭምር በትብብር እየተሰራበት ያለው ሰው ሰራሽ አስተውሎት በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ የመጀመሪያው የሆነውን የመደመር ሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ እያቋቋመች ነው፡፡
ኢትዮጵያ የባለሙያዎችን አቅም በማጎልበት መሰረታዊ የዲጂታል መሰረተ ልማቶችን በመገንባት ላይ ትገኛለች፡፡