የኢትዮጵያ ብሔራዊ የአደጋ ጊዜ ሕክምና ቡድን የዓለም ጤና ድርጅት ደረጃ አንድ ዓለም አቀፍ እውቅና አገኘ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ የአደጋ ጊዜ የሕክምና ቡድን የዓለም ጤና ድርጅት ደረጃ አንድ ዓለም አቀፍ እውቅና አግኝቷል።
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ 7ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የድንገተኛ ሕክምና ቡድኖች ዓለም አቀፍ ጉባኤ እየተካሄደ ነው።
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ቡድኑ በአፍሪካ ቀጣና የመጀመሪያው ሲቪል እና በሁሉም የዝግጁነት መስፈርቶች የተሟላ ሁለተኛው ቡድን በመሆን ታሪካዊ ምዕራፍ አስመዝግቧል።
ኢትዮጵያ የአደጋ መከላከል የሕክምና ድጋፍ ቡድንን በ2018 ዓ.ም ካቋቋመች ወዲህ ከ15 በላይ የሀገር ውስጥ ተልዕኮዎችን በማካሄድ እና ከ600 በላይ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን በማሰማራት አህጉራዊ አጋርነቷን ማሳየቷን ገልጸዋል።
እውቅናው የመጨረሻው ስኬት ሳይሆን በቀጣይም ዝግጁነትን ለማስቀጠል፣ ስልጠናዎችን ለመስጠት እና ከድንገተኛ አደጋዎች በፊት ሕዝብን የመድረስ አቅምን ለማጠናከር እንደሚሰራ አስረድተዋል።
የሕክምና ምላሽ እና የሕክምና ደህንነት ተለያይተው ሊታዩ እንደማይችሉ ገልጸው የማርበርግ እና የኢቦላ ወረርሽኞችን ለመከላከል የተደረገው ጥረት የጋራ ስኬትና የሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የሕዝብ ጤና አደጋዎች ማኔጅመንት መሪ ዶ/ር መልካሙ አብቴ በበኩላቸው÷ ጉባኤው በኢትዮጵያ መካሄዱ ለሀገሪቱ ትልቅ ኩራት መሆኑን ተናግረዋል።
ጉባኤው በእውቀት ልውውጥ፣ በትብብርና በጋራ ልምድ ማካፈል ላይ ያተኮረ እንደሆነ አንስተው የሕክምና ቡድኖቹ በወረርሽኞች፣ በተፈጥሮ አደጋዎችና በሌሎች የጤና ቀውሶች ወቅት ፈጣንና ወሳኝ አገልግሎት በመስጠት ረገድ የሕዝብ ጤና አደጋ ዝግጁነት ቁልፍ ምሰሶ እንደሆኑ አስረድተዋል።
ከጤና ሚኒስቴር፣ ከዓለም ጤና ድርጅትና ከሌሎች አጋሮች ጋር በተደረገ ቅንጅት ሀገራዊ የሕክምና ቡድኑ ወደ WHO Type-1 ደረጃ እንዲሸጋገር መደረጉን ጠቁመዋል።
እንዲሁም የ2025-2029 ስትራቴጂክ ዕቅድ እነዚህን ስኬቶች ለማጠናከርና ወደፊት ኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት የትብብር ማዕከል እንድትሆን ለማስቻል አልሞ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
እያንዳንዱ የአፍሪካ ሀገር እስከ 2030 ድረስ የተሟላ ብሔራዊ የድንገተኛ አደጋ ሕክምና ቡድን እንዲኖረው ያሳሰቡት ደግሞ የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር መሀመድ ያቁብ ናቸው።
መንግሥታት የገቡትን ቃልኪዳን በበጀት ወደተደገፉ ብሔራዊ ዕቅዶች እንዲለውጡ እና አፍሪካ ለችግሮቿ የራሷን መፍትሄ መስጠት እንዳለባት አፅንዖት ሰጥተዋል።
በሶስና አለማየሁ