Fana: At a Speed of Life!

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች የሚደረጉ ድጋፎች ይጠናከራሉ – የዓለም ባንክ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓለም ባንክ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አሳወቀ።
የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በጽህፈት ቤታቸው የዓለም ባንክ ተወካዮችን ተቀብለው አነጋግረዋል።
ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ ጋር የምትሰራቸው ሥራዎች ውጤታማ ናቸው።
በዋን ዋሽ ፕሮግራም አማካኝነት ለሌሎች ሀገራት ተሞክሮ የሚሆን ውጤታማ ሥራ ሰርተናል ያሉት ሚኒስትሩ ይህም ውጤት በመንግሥት ጠንካራ ክትትል የመጣ ነው ብለዋል።
የዓለም ባንክ ተወካዮች ቡድን መሪ ጁሊያን ቪክተር በበኩላቸው፤ ተቋማቸው ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በትብብር የሚሰራቸው ፕሮጀክቶች በጥሩ ሁኔታ እየሄዱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ መንግሥትና በልማት አጋሮች በጋራ የሚደገፈው የአንድ ቋት ብሔራዊ ዋሽ ፕሮግራም በንጹህ የመጠጥ ውሃ እና በሳኒቴሽን ከ10 ሚሊየን በላይ ሰዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን አንስተዋል።
በተመሳሳይ በከተሞች የሚገነቡ የፍሳሽ ዝቃጭ ማከሚያ ፕሮጀክቶች በተጠናከረ ክትትል እስከ ሰኔ ወር ድረስ 14 የማከሚያ ጣቢያዎች እንዲጠናቀቁ መስራት እንደሚገባ አንስተዋል።
በውይይቱ የገጠር የውሃ አቅርቦት ዲዛይን ማጠናቀቅ፣ የቀሩ የግንባታ ውሎችን መፈረም እና የፋይናንስ ክፍያን ማፋጠን ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ናቸው።
በቀጣይም የኢትዮጵያ መንግሥት እና ዓለም ባንክ የጋራ የትግበራ ድጋፍና ግምገማ ተልዕኮዎችን ለማካሄድ ተስማምተዋል።
ውይይቱ የፕሮጀክቶቹን አፈፃፀምም በቅርበት ለመከታተል፣ የሚታዩ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታትና የታቀዱ ውጤቶችን ለማሳካት የሚያግዝ እንደሆነም ተነስቷል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.