Fana: At a Speed of Life!

ከራስ አልፎ ለዓለም ገበያ፤ የኢትዮጵያ የስንዴ ምርት ስኬትና የምግብ ሉዓላዊነት ጉዞ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የምግብ ሉዓላዊነትን በተግባር እያረጋገጠች የምትገኘው ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እያሳየች የምትገኘው ስኬት የሀገሪቱን የልማት ጉዞ አዲስ ምዕራፍ እየከፈተ ይገኛል።
ለረጅም ዘመናት ኢትዮጵያ በስንዴ ፍላጎቷና በሀገር ውስጥ ምርቷ መካከል የነበረውን ክፍተት ለመሙላት ከውጭ ሀገራት ስንዴ ለማስገባት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለማውጣት ትገደድ ነበር።
ይህም በሀገሪቱ የንግድ ሚዛን ላይ ጫና በመፍጠር ለፈተናዎች ተጋላጭ እንድትሆን ያደርጋት ነበር። ይህንን ተግዳሮት ወደ ዕድል ለመቀየርም ከዓመታት በፊት የመደመር መንግሥት የለውጥ አቅጣጫ በመቀየስ ሰፊ የልማት እንቅስቃሴ ጀመረ።
በዚህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ተግባራዊ የሆነው የስንዴ ልማት የሀገሪቱን የስንዴ ምርት አቅም ከፍ በማድረግ በዘርፉ አዲስ የስኬት ታሪክ እንዲጻፍ አስችሏል።
ከዚህ ሥራ ፍሬዎች መካከል በዛሬው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ዞን የጎበኙት የክረምት ስንዴ እርሻ አፈጻጸም አንዱ ነው።
ይህ አዲስ አቅጣጫ በመስኖ ቴክኖሎጂ፣ በተሻሻሉ የስንዴ ዘሮች፣ በማዳበሪያ፣ በዘመናዊ የእርሻ ማሽነሪዎችና በተሻለ የአመራረት ሥርዓት የታገዘ ሲሆን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በርካታ አርሶ አደሮችን በልማቱ ቀጥታ ተሳታፊ አድርጓል።
ይህም የመሬትን ምርታማነት ከማሳደጉ ባሻገር የአርሶ አደሩን ገቢ ለማሳደግ፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የግብርና ምርትን በተረጋጋ ሁኔታ ለገበያ ለማቅረብ አስችሏል።
በተገኘው የስንዴ ምርት እድገትም ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከውጭ ሀገራት በከፍተኛ ወጪ ስታስገባው የነበረውን ስንዴ በሀገር ውስጥ በማምረት የራሷን ፍላጎት መሸፈን የሚያስችል አቅም ገንብታለች።
ከዚያም አልፎ ወደ ውጭ ገበያ ስንዴ ማቅረብ መጀመሯ የዚህ ለውጥ ተጨባጭ ማሳያ ሆኗል። ይህ ስኬት ስንዴን ከውጭ በማስገባት የሚታወቅ የነበረውን ሀገር ወደ ስንዴ ላኪነት መሸጋገር እንደሚቻል ያሳየ ታሪካዊ ለውጥ ነው።
በተጨማሪም የምግብ አቅርቦትን በማረጋጋት በዓለም ገበያ የሚከሰቱ የአቅርቦት ችግሮችና የዋጋ መዋዠቆች በሀገር ውስጥ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድሩትን ጫና ለመቋቋም ያግዛል።
ከዚህ ባሻገር የስንዴ ልማት በግብርናው ዘርፍ የተሻለ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የአሠራር ለውጥ እንዲመጣ አድርጓል።
ዛሬ በመደመር መንግሥት ታሪካዊ አቅጣጫ በስንዴ ምርት ከራሷ ፍላጎት አልፋ ወደ ውጭ ገበያ መድረስ የቻለችው ኢትዮጵያ፣ ነገም በሌሎች የግብርና ዘርፎች ተመሳሳይ ውጤት ለማስመዝገብ ያላትን እምቅ አቅም እያሳየች ነው።
ይህ ጉዞ በስንዴ ምርት የተጀመረ ቢሆንም መዳረሻው ግን ከዚያ የሰፋ ነው፤ በራሷ አቅም የምትበለጽግ፣ የምግብ ፍላጎቷን በራሷ የምትሸፍንና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት የምታቀርብ ሀገር እውን ማድረግ የተቀመጠ ርዕይ ነው።
በመልካም ፈቃዱ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.