የ2ኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ተሳታፊዎች የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤትን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የ2ኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ተሳታፊዎች በአዲስ አበባ እያካሄዱት ከሚገኙት አህጉራዊ ጉባኤ ጎን ለጎን የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤትን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት የብልጽግና ፓርቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ስሁል ለልዑካን ቡድኑ ገለጻ አድርገዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ የፓርቲውን የአደረጃጀት፣ የፖለቲካና የሪፎርም ሥራዎች እንዲሁም በመደመር ፍልስፍና ኢትዮጵያ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች እያስመዘገበች የምትገኘውን ዘለቄታዊ ስኬቶች አብራርተዋል።
የጉባኤው ተሳታፊዎች በጽሕፈት ቤቱ ባደረጉት ቆይታ የፓርቲውን አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ፣ ዘመናዊ የአሠራር ዘይቤዎችና የዲጂታል አደረጃጀቶች ተመልከተዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለውን አህጉራዊ ትብብርና ሁለገብ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ቁልፍ የጋራ ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ የሃሳብ ልውውጥ ተካሂዷል።
የጉባኤው ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ መሰል የልምድ ልውውጦች በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን የፖለቲካና የልማት ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የአፍሪካ ፖለቲካ ጉባኤ በአህጉሪቱ በሚገኙ ልዩ ልዩ የፖለቲካ ድርጅቶችና አመራሮች መካከል ትብብርን ለማጠናከር፣ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ለማፋጠንና የወደፊት የአፍሪካን የጋራ ልማት ለመቅረጽ የሚያስችል ዋና መድረክ መሆኑ ይታወቃል።