ወታደራዊ ስልጠና ለላቀ የአመራር ብቃት
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የመንግስት አመራሮች ወታደራዊ ስልጠናዎችን እንዲወስዱ እና የደህንነት ፖሊሲዎችን በአግባቡ እንዲረዱ እያደረገ ነዉ፡፡
አሁን ላይ በፌደራል ደረጃ የሚገኙ የፖለቲካ አመራሮች ይወስዱ የነበረውን ስልጠና በማጠናቀቅ ወደ ስራ ገበታቸው ተመልሰዋል፡፡
ይህ የአጭር ጊዜ የወታደራዊ ስልጠና ትምህርት በብዙ ሀገራት የፖለቲካ አመራሮች የወታደራዊ ስትራቴጂን ጨምሮ የደህንነት ፖሊሲን በአግባቡ እንዲረዱ የሚደርግ ሥልጠና ነው።
ይህን ከሚሰጡ ሀገራት መካከል አሜሪካ፣ ቻይና፣ ዪናይትድ ኪንግደም እና ሕንድ ተጠቃሾች ሲሆኑ
እንደ እስራኤል፣ ስዊዘርላንድ እና ሰሜን ኮሪያ ያሉ ሀገራት ደግሞ ፖለቲከኞቻቸው የወታደራዊ ልምድ እንዲኖራቸው የሚያደርግ አሰራርን ይከተላሉ፡፡
ኢትዮጵያም ይህን ልምድ በመውሰድ ለከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮችዋ ስልጠናዎችን እየሰጠች ነው፡፡ በፌደራል ደረጃ የሚገኙ ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮች ስልጠናውን ወስደው አጠናቀው ወደ ስራቸው ተመልሰዋል ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የስልጠናውን መጠናቀቅ ተከትሎ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የወታደራዊ ሳይንስ ሥልጠናው በአካላዊ፣ በአእምሯዊና በተግባር ዝግጁነት ረገድ አዲስ አቅም ያስጨበጠ ነው ብለዋል፡፡
የወታደራዊ ሳይንስ ስልጠናው ለሲቪል አመራሮቹ መሰጠቱ ስለ ወታደራዊ አስተሳሰብ፣ ስለ መከላከያ ሥርዓት፣ ስለ ሀገራዊ ደህንነት እና ስለ ስትራቴጂካዊ ውሳኔ አሰጣጥ ያላቸውን ግንዛቤ ለማስፋት ጠቃሚ መሰረት እንደፈጠረም አስረድተዋል።
ይህ ስልጠና አመራሮቹ ከነበራቸው የሥራ ባህል በተጨማሪ የወታደራዊ የሥራ ባህልና ሀገር ወዳድነትን እንዲሁም እየሞቱ ሀገርን የማፅናት የውትድርና ሙያን ለመገንዘብ የሚረዳ ነው፡፡
በሁርሶ የዕጩ መኮንኖች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለከፍተኛ የሀገሪቱ አመራሮች የተሰጠው ስልጠና የተቋሙን የማሠልጠን አቅምና ልምድ ከማሳየት አልፎ አመራሮቹ በስልጠናው ያገኙት ተሞክሮ የመከላከያ ሠራዊቱን ተግባርና ኃላፊነት በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት እንዲሁም በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የተቀናጀ አመራርን ለማጠናከር ያግዛቸዋል፡፡
ይህን እውቀት ተጠቅሞ የሀገርን እድገት ለማፋጠን እና የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በተቀናጀ መልኩ በጋራ ለመስራት የወታደርን ዲሲፕሊን ተግባር ላይ ማዋል እንደሚገባ ማሳያ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የኢኮኖሚ ቁንጮ የመሆን ጉዞዋን ለማሳለጥ የጀመረቻቸው ሥራዎች ለማሳካት ትክክለኛው መንገድ ላይ መሆንዋንም ማሳያዎች ናቸው፡፡
በእመቤት ሲሳይ