ሁለቱ የውሃ አካላት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ብልጽግና
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ከጥንት ጀምሮ የሀገራት ስልጣኔ እና እድገት ከውሃ አካላት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ህልውና እና የቀጣይ ዘመን ብልጽግናም ከታላላቅ የውሃ አካላት ጋር ባለው የጠበቀ ቁርኝት ላይ የተመሰረተ ሲሆን፤ በተለይም ዓባይ እና ቀይ ባህር የዚህች ጥንታዊት ሀገር ኢኮኖሚያዊ እና ጂኦፖለቲካዊ እስትንፋሶች ሆነው ዘመናትን ተሻግረዋል።
ኢትዮጵያ ከ76 በመቶ በላይ የሚሆነውን የዓባይ ውሃ አመንጭታ ለሰሜን አፍሪካ ስትሰጥ የኖረች ብትሆንም፤ ይህን ተፈጥሯዊ ሀብቷን ለራሷ ልማትና ለህዝቦቿ ብልጽግና ሳታውል ለረጅም ዘመናት በቁጭት ስትታዘብ ቆይታለች።
ይሁን እንጂ ዘመናትን የተሻገረው ይህ ቁጭትና የልማት ጥያቄ በጽናትና በህዝባዊ አንድነት ተቀይሮ ሀገሪቱ በራሷ አቅሟና በዜጎቿ አስተዋጽኦ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እውን ማድረግ ችላለች።
ይህ ታላቅ ፕሮጀክት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ብቻ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያውያን ተባብረው ከተነሱ የማይሻገሩት ፈተና አለመኖሩን ለዓለም ያረጋገጡበት ሆኗል።
የህዳሴውን ግድብ እውን የማድረግ ጉዞ ግን አልጋ በአልጋ አልነበረም። ሀገሪቱ በሂደቱ ውስጥ በርካታ ውስብስብ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ፈተናዎችን ተጋፍጣ አልፋለች።
በተለይም የእኔ ብቻ ልደግ አስተሳሰብ አሁንም ያልለቀቃቸው የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ማጠናቀቂያው ድረስ የተለያዩ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ትንኮሳዎችን አድርገዋል፡፡
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት በተከተሉት ጽናት ላይ የተመሰረተ መርህ የውጪ ጫናዎችንና እንቅፋቶችን በመመከት ፕሮጀክቱን ወደ ፍጻሜ ማድረስ ተችሏል።
ኢትዮጵያ ይህን ታላቅ የውሃ ሀብቷን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በመጠቀም ለቀጣናዊ የኃይል ትስስርና ብልጽግና በር ከመክፈቷም ባሻገር፤ የተፈጥሮ ሀብቷን ለመጠቀም የየትኛውንም አካል ፈቃድ መጠየቅ እንደማያስፈልጋት በተግባር አስመስክራለች።
ዓባይን በጽናትና በድል የተሻገረችው ኢትዮጵያ አሁን ደግሞ እይታዋን ወደ ሌላኛው የታሪክና የህልውናዋ መሰረት ወደሆነው ቀይ ባህር አዙራለች።
በሴራ ፖለቲካ ምክንያት የራሷን የባህር በር ያጣችው ኢትዮጵያ ሰፊ ህዝቧን ለማስተዳደርና ኢኮኖሚዋን በዘላቂነት ለማሳደግ የባህር በር አስፈላጊነትን ተረድታለች።
በመሆኑም ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ህጎችና በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ ሰላማዊ አካሄድን በመከተል የባህር በር ጥያቄዋን እያንጸባረቀች ትገኛለች።
ይህ ጥያቄ የሌሎችን ሀገራት ሉዓላዊነት በመጋፋት ሳይሆን፤ በቀጣናው ላይ የጋራ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያስገኝ፣ የንግድ ትስስርን የሚያጠናክርና ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደርግ የጋራ ብልጽግና ርዕይ ነው።
ከዚሁ ጎን ለጎን ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የምታደርገውን ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ በተግባር እያሳየች ትገኛለች።
ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ መባባስ ቀጥተኛ ተጠያቂ ባትሆንም፤ ችግሩን ለመከላከልና የተፈጥሮ ሚዛንን ለመጠበቅ ከ56 ቢሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል ታሪክ እየሰራች የአረንጓዴ ዐሻራ እያሳረፈች ትገኛለች።
ይህ ጥረት ዓባይን ጨምሮ ታላላቅ ወንዞች እንዳይነጥፉና የአካባቢው ስነ-ምህዳር እንዲጠበቅ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ፤ ሀገሪቱ ለቀጣናውም ሆነ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የምታበረክተው አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማረጋገጫ ነው።
ዓባይና ቀይ ባህር ለኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታና ዘላቂ ብልጽግና ወሳኝ የሆኑ ሁለት የህልውና አምዶች በመሆናቸው፤ ሀገሪቱ በፍትሃዊነትና በጋራ እድገት መርህ ላይ ተመስርታ የምታደርገውን የልማት ጉዞ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በበጎነት ሊደግፈውና ሊቀበለው ይገባል።
በእመቤት ሲሳይ