Fana: At a Speed of Life!

ለኮፕ – 32 ጠንካራ ዝግጅት ላይ የምትገኘው የኢትዮጵያ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በቀጣዩ ዓመት የሚካሄደውን የኮፕ – 32 ለማዘጋጀት የተለያዩ ዝግጅችን እያደረገች የምትገኘው ኢትዮጵያ ለጉባኤው ዝግጁ መሆኗን በኮፕ – 31 መድረክ ላይ እያስመሰከረች ትገኛለች፡፡
ከ60 በላይ ዝግጅቶችን የምታቀርበበትን ፓቪሊዮን በቱርኪዬ አንታሊያ በተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ የከፈተችው ኢትዮጵያ ለኮፕ – 32 ጉባኤ ያለችበትን የዝግጁነት ደረጃ እያሳየች ነው፡፡
የኢትዮጵያ ፓቪሊዮን ኢትዮጵያን ለዓለም በሰፊው ለማሳየት እና የኮፕ – 32 ዝግጅትን ለማጉላት ያለው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡
በቱርኪዬ አንታሊያ እየተካሄደ ያለው የኮፕ – 31 ጉባኤ ኢትዮጵያ ዓለም ሊተማመንባት የምትችል እና ለኮፕ – 32 ጠንካራ ዝግጅት እያደረገች የምትገኝ ሀገር መሆንኗን ማሳያ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
መድረኩ ወዳጅነትን የምናፈራበት፣ ኢንቨስትመንቶችን የምንስብበት ለስራው የሚሆን የፋይናንስ ድጋፍ ለማግኘት የምንነጋገርበት፣ አጋርነት የምንፈጥርበት በአጠቃላይ ኢትዮጵያን ከፍ የሚያደርግ እና የሚመጥን እንዲሁም ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተቻቸውን የስልጣኔ፣ የምርት እና የማዕድን ሀብቶች የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
ከ56 ቢሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ የራሷን አስተዋጽኦ እያበረከተች የምትገኘው ኢትዮጵያ ራሷ የአየር ንብረት ለውጥ ተጠቂ ሆና ዓለም የሚሰጣት ማካካሻ ባይኖርም በራሷ አቅም ለአየር ንብረት ለውጥ አስተዋጽኦ እያደረገች እና አሻራዋን እያስቀመጠች ነው፡፡
ይህ የኮፕ – 31 መድረክ ኢትዮጵያ ደምቃ እየታየችበት ያለ እና ለጉባኤ እና ለስብሰባዎች ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ለቱሪዝም እና ለሌሎችም ዝግጅቶች ተመራጭ ሀገር መሆኗን በዓለም መድረክ ለማስተዋወቅ እየተሰራበት ያለ ነው፡፡
ኮፕ – 31 ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ስለምታደርገው እንቅስቃሴ ዓለም እንዲያውቅ ለማድረግ ያግዛል ያሉት ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኮፕ – 32 ጉባኤን በከፍተኛ ጉጉት እንዲጠብቅና በቁጥር ሰፊ የሆነ ታዳሚ በጉባኤው ላይ እንዲገኝ የማድረግ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ኮፕ – 31 ላይ ማሳካት የምንፈልጋቸው ግቦች አሉ ብለዋል፡፡
በኮፕ – 31 የሚኖረው የድርድር ሂደት ውጤታማ ሆኖ ለኮፕ – 32 ስኬት ጠንካራ መሰረት እንዲጥል ማድረግ ዋነኛው ግብ እንደሆነ አንስተው፤ ይህንን ለማሳካት ከቱርኪዬ እና አውስትራሊያ ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ታዲያ ይህ መድረክ በተለያዩ ዘርፎች ኢትዮጵያ ለኮፕ – 32 ጉባኤ ብቁ መሆኗን እያስመሰከረች የምትልዘልቅበት እንደሆሚሆንም ይጠበቃል፡፡
በእመቤት ሲሳይ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.