Fana: At a Speed of Life!

የሀገር ውስጥ ምርት ስሌትን ማዘመን የኢኮኖሚውን እውነተኛ አቅምና እድገት በትክክል ለመለካት ያስችላል

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገር ውስጥ ምርት ስሌትን ማዘመን የኢኮኖሚውን እውነተኛ አቅም፣ አፈጻጸምና መዋቅራዊ ሽግግር በትክክል ለመገምገም ያስችላል አሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዘመዴነህ ንጋቱ።
የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስቴር የተሻሻለውን ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ግመታን ወቅታዊ የማድረግ ሥራ ይፋ የተደረገ ሲሆን በዚህም የተሻሻለው ጠቅላላ የሀገር ውስጥ መረጃ ቋሚ ዓመት ከ2008 ወደ 2017 ዓ.ም እንዲቀየር ተደርጓል።
በዚህም የጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ቋሚ ዓመት ለውጥ ወቅታዊ ግምት መሰረት ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርቱ 59 ነጥብ 2 በመቶ አድጓል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ዘመዴነህ ንጋቱ እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያስመዘገበውን ፈጣን እና ሁለገብ ዕድገት ትክክለኛ መዋቅራዊ ገጽታ ለማሳየት፣ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ስሌት መለኪያ ማሻሻያ መደረጉ ተገቢነት ያለው ነው።
ቀደም ሲል ጥቅም ላይ ይውሉ የነበሩት መለኪያዎች የተዋቀሩት ሀገሪቱ በግብርናው ዘርፍ ብቻ ጥገኛ በነበረችበት ወቅት እንደነበር በማንሳት በአሁኑ ወቅት ሌሎች ዘርፎች እያስመዘገቡት ያለውን ግዙፍ እምቅ አቅም እና አስተዋጽኦ ያላካተቱ በመሆናቸው፣ ወቅታዊውን ሀገራዊ የኢኮኖሚ እውነታ በሚገባ እንደማያሳዩ አስረድተዋል።
ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ያስመዘገቡ ሌሎች የዓለም አቀፍ ሀገራትም ኢኮኖሚያቸውን በዘመናዊ መልኩ መለካት የተለመደ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የደረሰበትን እውነተኛ ዕድገት የሚመጥን እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የሀገር ውስጥ ምርት ስሌት መለኪያ ማሻሻያ መደረጉ ተገቢነት ያለው መሆኑን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዘርፎችን አፈጻጸም በዘመናዊ መንገድ በመለካት የዕድገት አስተዋጽኦቸውን ለመገምገም እና ትኩረት የሚሹ መስኮችን በቀላሉ ለመለየት የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።
በተለይም ሀገራችን በኢኮኖሚ ልማት እያስመዘገበችው ያለውን እውነተኛ ገጽታ በግልጽ በማሳየት በውጭ ባለሀብቶች ዘንድ ትልቅ መተማመን በመፍጠር የኢትዮጵያን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ መዳረሻ እንድትሆን ሰፊ በር የሚከፍት ከመሆኑም በላይ አጠቃላይ የዕዳ ጫናን አቀናጅቶ በመቀነስ ረገድ የጎላ ድርሻ እንዳለው አመልክተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የታክስ ሥርዓቱን በማዘመን እና የግብር መሰረቱን ለማስፋት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.