Fana: At a Speed of Life!

ለብሔራዊ ጥቅም የቆመው የዓባይና ቀይ ባሕር ፎረም

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ህልውና ከዓባይ ወንዝና ከቀይ ባሕር ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። እነዚህ ሁለት የውሃ አካላት በርካታ ሀገራትን የሚያገናኙ እንዲሁም የተለያዩ ፍላጎቶች የሚንጸባረቁባቸው የትብብር ብሎም የግጭት መነሻዎች ናቸው።

የዓባይ ወንዝን ጉዳይ በተመለከተ የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ የተፋሰሱን ሀገራት የልማት ፍላጎትና የጋራ ጥቅም ባገናዘበ መልኩ የጋራ የውሃ ሀብትን በፍትሃዊነትና በዘላቂነት ለማስተዳደር ይሠራል።

ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ የውጭ ንግድ፣ የወደብ አገልግሎት፣ የሎጂስቲክስ፣ የኢኮኖሚ፣ የደህንነትና የቀጣናዊ ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው።

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በንግድና በማጓጓዣ ቅልጥፍና ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው ከመሆኑም በላይ ሀገሪቱ ከዓለም ኢኮኖሚ ጋር ያላትን ትስስር እንዲሁም ብሔራዊ ደህንነቷን የሚወስን ጉዳይ ነው።

ለዚህም በዓባይ ወንዝና በቀይ ባሕር ላይ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በሳይንሳዊ ጥናት፣ በምርምር፣ በፖሊሲ ውይይትና በዲፕሎማሲያዊ ጥረት ለማጠናከር የሚያግዝ፤ ምሁራንን እና ሲቪል ማኅበረሰብን ያካተተ የዓባይና ቀይ ባሕር ፎረም ተቋቁሟል።

የዓባይና ቀይ ባሕር ስትራቴጂያዊ ፎረም በተለያዩ የሙያና የትምህርት ዘርፎች በተውጣጡ ምሁራን የተቋቋመ ሲሆን፣ ሕጋዊ እውቅና ካገኘ በኋላ የሚያከናውናቸውን ቀጣይ ሥራዎች ይፋ አድርጓል።

ፎረሙ በዓባይ እና ቀይ ባሕር ጉዳይ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስጠበቅ የሚደረገውን ሀገራዊ ጥረት በሙያዊ እውቀትና በጥናት ለመደገፍ ያለመ ነው።

የዓባይ ወንዝና የቀይ ባሕር ጉዳዮች ከተፈጥሮ ሀብት አስተዳደር ባለፈ ከኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ብሔራዊ ፀጥታ፣ የውጭ ንግድ፣ ቀጣናዊ ትስስር እንዲሁም ጂኦፖለቲካዊ ፍላጎት ጋር በቀጥታ የተያያዙ ናቸው።

ስለሆነም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የሚካሄዱ ውይይቶች በታሪካዊ ማስረጃዎች፣ በዓለም አቀፍ ሕጎችና መርሆዎች፣ በመልክዓ ምድራዊ እውነታዎችና በኢኮኖሚያዊ መረጃዎች የተደገፉ መሆን ይኖርባቸዋል።

ፎረሙ የአባይ ወንዝና የቀይ ባሕርን ታሪካዊ፣ ሕጋዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ መልክዓ ምድራዊና ጂኦፖለቲካዊ ጉዳዮች በማጥናት ለመንግሥትና ለፖሊሲ አውጪዎች ሙያዊ ግብዓት በማቅረብ ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን አልምታ የመጠቀም መብቷን በሚደግፉ ሳይንሳዊና ሕጋዊ መረጃዎች ላይ በመመርኮዝ ፍትሃዊና ምክንያታዊ አጠቃቀምን ያበረታታል።

ሌላው ለኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት ያለውን የንግድ፣ የኢኮኖሚና የቀጣናዊ ትስስር ፋይዳ በጥናት በማስደገፍ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግንዛቤ በመፍጠር ከተለያዩ ሀገራት፣ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ጥቅም፣ በሰላማዊ ውይይትና በትብብር ላይ የተመሠረተ ግንኙነቶችን ለመገንባት የሚያስችሉ መላዎችን ይዘይዳል።

የፎረሙ መቋቋም ከሁለቱ ወሳኝ የተፈጥሮና የጂኦፖለቲካ ሀብቶች ጋር በተያያዙ ጉዳዮች የምሁራን፣ የተመራማሪዎች፣ የመንግሥትና የሲቪል ማኅበረሰብን የጋራ ተሳትፎ ለማሳደግ ይሠራል።

ሀገራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ተግባር በዕውቀት፣ በመርህ፣ በመረጃ እና በዓለም አቀፍ ሕግ ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ አሠራር መደገፍ ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ ፎረሙ በምርምር የተደገፉ ሐሳቦችን ወደ ፖሊሲ ውይይት በማምጣት ለሀገራዊ ውሳኔዎች የሙያ ድጋፍ ያበረክታል።

በተለይም የባህር በር ጉዳይና የዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ከተቀናቃኝነትና ግጭት በመራቅ ወደ የጋራ ልማት፣ የኢኮኖሚ ትስስርና ቀጣናዊ መረጋጋት ምንጭነት መለወጥ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት ነው።

የአባይና ቀይ ባሕር ፎረም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በእውቀት፣ በምርምርና በሰላማዊ ዲፕሎማሲ ለማስጠበቅ የሚደረገውን ጥረት በማጠናከር በሚያቀርባቸው የጥናት ውጤቶችና የፖሊሲ አማራጮች ቀጣናዊ የትብብር ግንኙነቶች ያጠናክራል።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በምህረት ደምሴ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.