Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ተጨባጭ ለውጥ እያስመዘገበች ነው – ምሁራን

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከካርቦን ልቀት ነፃ የሆነ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት በያዘችው ሀገራዊ እቅድ ተጨባጭ ለውጥ እያስመዘገበች ነው አሉ የዘርፉ ምሁራን፡፡

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ ሳይንስና የሥነ-ሰብ ኮሌጅ የሥነ-መንግሥትና የልማት ጥናት መምህርና ተመራማሪ ጣሰው ታደሰ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት፤ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ የምግብ ሉዓላዊነትና የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያስተሳሰረ ይገኛል።

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባኤን (ኮፕ-32) ለማስተናገድ መመረጧ በአረንጓዴ ልማትና በአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ያላትን አስተዋጽኦ የሚያረጋግጥ ታሪካዊ ዕድል ነው ብለዋል።

ጉባኤው በኢትዮጵያ መካሄዱ ሀገሪቱ የአየር ንብረት ተጽዕኖን ለመከላከል ላከናወነቻቸው ተጨባጭ ተግባራት እውቅና የሰጠ መሆኑንም አንስተዋል።

የታዳሽ ኃይል ልማትን ከቃል ኪዳን ወደ ተግባር በመቀየር ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነውን የኤሌክትሪክ ኃይል ከታዳሽ ኃይል ምንጮች እንደምታመነጭ ተናግረዋል።

ለዚህም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጨባጭ ማሳያ መሆኑን ገልጸው፤ ለጎረቤት ሀገራት የታዳሽ ኃይል ኤሌክትሪክ በማቅረብ ቀጣናው ከካርቦን ልቀት የፀዳ እንዲሆን የበኩሏን ድርሻ እየተወጣች ትገኛለች ነው ያሉት።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ ተባባሪ ፕሮፌሰር ተራማጅ ተሰፋዬ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ተጽዕኖን በመቋቋም የሠራችውን ተጨባጭ ሥራ በአግባቡ ማስተዋወቅና መሸጥ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ባከናወነቻቸው ተግባራዊ እርምጃዎች የኮፕ-32 አስተናጋጅ ሆና መመረጧን ገልጸው፤ አጋጣሚውን በመጠቀም ዓለምን ስለ አየር ንብረት ልናስተምር ይገባል ብለዋል።

በዚህ ረገድ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለአየር ንብረት ቀውስ አይነተኛ ምላሽ ሆኖ የሚጠቀስ ተሞክሮ መሆኑንና በዚህም በርካታ ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ ሥራ ላይ ተከታታይነት ያላቸውን ሥራዎች እየሠራች መሆኗን አንስተው፣ በዚህም የአካባቢ ሥነ-ምህዳር ተስተካክሎ መሬት ማገገሙንና የግብርና ምርትና ምርታማነት መጨመሩን ጠቁመዋል፡፡

እንዲሁም ወጣቶች በማኅበር ተደራጅተው የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸው፤ እንደ ሀገር የተሠራውን ሥራ ለዓለም በማሳየት ሀገራችንን የማስተዋወቅና የመሸጥ ሥራ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

#ኢትዮጵያ #ኮፕ_32_ኢትዮጵያ #COP31 #COP32 #COP32ETHIOPIA #fanamediacorporation

በማቴዎስ ፈለቀ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.