የቀድሞ ታጣቂዎች አዲስ የሕይወት ጉዞ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በትግራይ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎችን ከትጥቅ ትግል ወደ ሰላማዊ ሕይወት በማሸጋገር በምርታማ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲሳተፉ ማስቻል ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝ ነው።
ይህም የቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶና መልሶ ማቋቋም ስልጠና ወስደው አዲስ የሕይወት አቅጣጫ እንዲይዙ፣ ሙያና ክህሎት እንዲያገኙ፣ የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩና እንደ ሌሎች ዜጎች በሀገራዊ ልማት እንዲሳተፉ የማስቻል እድል ነው።
የፌዴራል መንግሥት ስልጠና የወሰዱ የቀድሞ ታጣቂዎች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ካሉ የሥራ ዕድሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከሚመለከታቸው ተቋማትና አካላት ጋር በመተባበር ይሠራል።
በተለይም የሙያ ሥልጠና፣ የክህሎት ማሻሻያና ትስስር በመፍጠር የቀድሞ ታጣቂዎች ያላቸውን አቅም ወደ ምርታማነት እንዲቀይሩ ለማገዝ ዝግጁ ነው፡፡
ይህም የተሃድሶ ሂደቱ ከጊዜያዊ ድጋፍ ባለፈ ዘላቂ የኑሮ መሠረት የሚጥል ሲሆን፤ የሥራ ዕድል ፈጠራው የሰልጣኞችን ኢኮኖሚያዊ ነፃነት ከማጠናከሩም በላይ ወደ ማህበረሰቡ ለመቀላቀል፣ የራስ መተማመንን ለመመለስና የሰላም ግንባታን ለማጠናከር ያግዛል።
በክልሉ ስልጠና ያጠናቀቁ 7 ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎችን ጨምሮ ከ63 ሺህ 500 በላይ ሰልጣኞች በተሃድሶ ሂደቱ ተጠቃሚ ሆነዋል። ለሥራና ለአቅም ግንባታም 7 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር፣ ለምግብና ለአልባሳት ደግሞ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጪ ተደርጓል።
የተሳታፊዎችን የቀድሞ ሙያና የሥራ ልምድ በመለየት፣ ከገበያው ፍላጎት ጋር የተጣጣሙ ሥልጠናዎችን በመስጠትና የሥራ ዕድል ከሚፈጥሩ ተቋማት ጋር ማስተሳሰር ድጋፉን ወደ ዘላቂ የገቢ ምንጭነት መቀየር ያስችላል።
በዚህ ረገድ በቴክኒክና ሙያ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ ምርት፣ በግንባታ፣ በቱሪዝም እንዲሁም በአገልግሎትና ዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፎች የተለያዩ የስራ ድሎችን ሰልጣኞችን ተጠቃሚ ይሆናሉ።
የሥራ ፈጠራ ሥልጠና፣ የመነሻ ካፒታል፣ የብድር አገልግሎትና የቴክኒክ ድጋፍ በማቅረብ ተሃድሶ ያጠናቀቁ ዜጎች የራሳቸውን ንግድና ምርታማ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲጀምሩ ማስቻል የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ ነው።
በውጭ ሀገራት ያሉ የሥራ ዕድሎችን ማስፋትም ሌላው አማራጭ ሲሆን፤ ይህ የሚከናወነው በሕጋዊና በተደራጀ የሥራ ስምሪት ሥርዓት፣ በቋንቋና በሙያ ብቃት ማረጋገጥ እንዲሁም የሠራተኞችን መብትና ደህንነት በሚጠብቁ ስምምነቶች ላይ ይመሰረታል።
የተሃድሶ ሂደቱ የሥነ ልቦና ድጋፍን፣ የጤና አገልግሎትን፣ የማህበረሰብ ተቀባይነትንና የማህበራዊ ትስስርን ማጠናከርንም እንደማጠቃለሉ በግጭት ምክንያት የሻከሩ ግንኙነቶችን ማደስ፣ በማህበረሰቡና በቀድሞዎቹ ታጣቂዎች መካከል መተማመንን መገንባትና ሰላማዊ አብሮ የመኖር ባህልን ማጠናከር ለስልጠናው ዘላቂ ውጤት ወሳኝ መሰረቶች ናቸው።
የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደ ሰላማዊና ምርታማ ሕይወት ማሸጋገር ለግለሰቦች የኑሮ ለውጥ ከማምጣት ባለፈ የሀገርን የሰው ኃይል አቅም ወደ ልማት የሚቀይር ትልቅ ሀገራዊ ኢንቨስትመንት ነው።
የሥራ ዕድል ሲፈጠር፣ የምርት አቅም ሲጨምር፣ የማኅበረሰብ ትስስር ሲጠናከርና የኑሮ ዋስትና ሲሻሻል የሰላም መሠረትም ይበልጥ ይጠናከራል።
ይህም የሰላምን ትርጉም በተግባር የሚያሳይ፣ የሰው ኃይልን ወደ ምርት የሚቀይርና ለተሻለ ሀገራዊ ብልጽግና መንገድ ይከፍታል።
በምሕረት ደምሴ