በጥቅምት ወር ከ66 ሺህ በላይ አዳዲስ ደንበኞች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሆኑ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 15፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2019 በጀት ዓመት ጥቅምት ወር ብቻ 66 ሺህ 473 አዳዲስ ደንበኞችን ከኤሌክትሪክ መረብ ጋር በማገናኘት የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሆነዋል አለ።
በወሩ 88 ሺህ 253 አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ 75 ነጥብ 3 በመቶ የሚሆነው ዕቅድ መሳካቱን የተቋሙ ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ አንዋር አብራር ለፋና ዲጂታል ገጸዋል፡፡
የወሩ አፈጻጸም ከ2018 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 20 ሺህ 23 ተጨማሪ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ያሳያል።
በወሩ አዲስ ከኤሌክትሪክ መረብ ከተገናኙት ደንበኞች መካከል 62 ሺህ 574 የሚሆኑት የቅድመ ክፍያ ቆጣሪዎች፣ ቀሪዎቹ 3 ሺህ 899 ደግሞ የድኅረ ክፍያ ቆጣሪዎች እንደተገጠመላቸው አመልክተዋል።
ከጠቅላላው አዲስ ደንበኞች ውስጥ 92 ነጥብ 3 በመቶ በኦፖሬሽን የተስተናገዱ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ 7 ነጥብ 7 በመቶ ደንበኞች ደግሞ በፕሮጀክት አማካኝነት አገልግሎቱን አግኝተዋል።
እስከ 2019 በጀት ዓመት ጥቅምት ወር መጨረሻ ድረስ የተቋሙ አጠቃላይ ደንበኞች ቁጥር 6 ሚሊየን 90 ሺህ 965 ደርሷል።
የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ማሳደግና ዜጎች ዘመናዊ የኃይል አገልግሎትን እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን የገለጸው ተቋሙ፤ የአዳዲስ ደንበኞች የኃይል ማገናኘት ሥራ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ከማሻሻል ባለፈ ለሀገራዊ ልማት ወሳኝ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብሏል።
በመሆኑም ተቋሙ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማስፋትና የኃይል አገልግሎትን ለዜጎች የማዳረስ ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል።