ብሪታንያ የአውሮፓ ህብረት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ካልቻለች ያለ ስምምነት ለመለያየት እንደማታቅማማ ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብሪታንያ የብሪግዚት ዋና አደራዳሪ ከአውሮፓ ህብረት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ካልቻለ ብሪታንያ ከህብረቱ ያለ ስምምነት ለመለያየት እንደማታቅማማ ገለጹ፡፡
ዴቪድ ፍሮስት ለሜይል ጋዜጣ እንደተናገሩት የሀገራቸውን ድንበር ዳግም መቆጣጠር ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ መሆኑን ነው ያነሱት፡፡
በዚሁ ጉዳይ ለመምከር የህብረቱ ተደራዳሪ ማይክል በርኔር ጋር ነገ በለንደን ለስምንተኛ ጊዜ ውይይት እንደሚያደርጉ ተሰምቷል፡፡
ብሪታንያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር በይፋ ፖለቲካዊው ፍቺ የፈጸመችው ጥር 23 እንደነበር ይታወሳል፡፡
በቀሪ የኢኮኖሚ፣ የድንበር እና በጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ለአስራ አንድ ወራት ሲያካሂዱት የነበረው ስምምነት መቋጫ ያለማግኘቱ እየተነገረ ነው፡፡
ህብረቱ የሽግግሩ ወቅት ከማብቃቱ በፊት ከብሪታንያ ጋር ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚፈልግ ይፋ አድርጓል፡፡
ሆኖም የእስከአሁኑ ድርድር ፍሬያማ ባለመሆኑ ሁለቱ ወገኖች ያለስምምነት እንደሚለያዩ እየተነገረ ይገኛል፡፡
ምንጭ፦አልጀዚራ