Fana: At a Speed of Life!

ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ከደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ልዩ መልእክተኛ እና የኢፌዴሪ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ከደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ጋር ተወያዩ።

በደቡብ ሱዳን ጁባ በተካሄደው ውይይትም የሁለቱን ሀገራት ፍላጎት በሚያሟላ መልኩ መንገድና ኤሌክትሪክን ጨምሮ ሀገራቱ በጥምረት በሚሰሯቸው ሌሎች የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ዙሪያ ተወያይተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ልዩ መልእክተኛ እና የኢፌዴሪ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ከውይይቱ በኋላ፥ በኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን መካከል የሚካሄዱ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች እውን እንዲሆኑ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንታዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ንሂያል ደንግንሂያል ውይይቱን ተከትሎ በሰጡት መግለጫ፥ የጋምቤላ-አኮቦ-ቦር የመንገድ ፕሮጀክትን በጥምረት መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከስምምነት ለመድረስ የደቡብ ሱዳን የመንገድና ድልድዮች ሚኒስቴር የኢትዮጵያ አቻው የቴክኒክ ቡድን ወደ ጁባ እንዲልክ ግብዣ እንደሚልክ አስታውቅዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም በውይይቱ ወቅት ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን በተለያዩ መሰረተ ልማቶች ዙሪያ በትኩረት በመስራት የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን የበለጠ የሚያጠናክሩበት እና ቀጠናዊ ኢኮኖሚያዊ ውህደትን እውን የሚያደርጉበት ወቅት አሁን ነው ማለታቸውንም ገልፀዋል።

በደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንታዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ንሂያል ደንግንሂያል የተመራ ልኡክ ባሳለፍነው ነሃሴ 25 ቀን 2012 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጋር ተወያይተው ነበር።

በውይይታቸውም ሀገራቱን በመንገድ እና በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ማስተሳሰር እንዲሁም የጋምቤላ-አኮቦ-ቦር የመንገድ ፕሮጀክትን በጥምረት መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸው ይታወሳል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.