የሀዋሳ ከተማ ም/ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ በከተማዋ ለሚገኙ 110 አካል ጉዳተኛና አቅመ ደካማ ነዋሪዎች የአዲስ ዓመት ስጦታ አበረከቱ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሀዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ በከተማዋ ለሚገኙ አንድ መቶ አስር አካል ጉዳተኛና አቅመ ደካማ ነዋሪዎች የአዲስ አመት ስጦታ አበረከቱ።
አቶ ጥራቱ ከተማ አስተዳደሩ ከባለሃብቶች ጋር በመሆን ያዘጋጀውን 1 ሺህ በጎችንና ምግብ ነክ ድጋፍ ለዘመን መለወጫ በስጦታ ለነዋሪዎቹ ለግሰዋል።
ምክትል ከንቲባው ከአስተዳደር ሉዑካቸው ጋር ቤት ለቤት በመንቀሳቀስም “እንኳን አደረሳችሁ” ብለዋል።
ድጋፉ ስር ከሰደዱ ማህበራዊ ችግሮች ጋር ተዳምሮ የኮቪድ-19 በከተማዋ አቅመ ደካማ ነዋሪዎች ላይ የፈጠረውን ተፅዕኖ ለመቀነስም ታስቦ መሆኑን ተናግረዋል።
በአዲሱ ዓመት የከፋ የጤና ችግር ያለባቸውን ነዋሪዎች የህክምና አገልግሎት ለመስጠትና ቤት የማደስ ተግባርም ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል አቶ ጥራቱ።
ከተማ አስተዳደሩ ለነዋሪዎች ያደረገውን ድጋፍ በማሰባሰብና በማስተባበር አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሃዋሳ ከተማ ባለሃብቶችም ምስጋና አቅርበዋል።
ሀዋሳ ሁሉም ብሔርብሄረሰቦች ተሳስበውና በፍቅር የሚኖሩባት ከተማ ናት ያሉት ምክትል ከንቲባው፥ የ2013 አዲስ አመት ሁሉም የከተማዋ ነዋሪዎችና ኢትዮጵያዊያን ተሳስበው እንደ ሃገር ውጤታማ የሚሆኑበት ዘመን እንዲሆን መልካም ምኞት መልዕክትም አስተላልፈዋል።
በሶዶ ለማ