Fana: At a Speed of Life!

ዓመቱ በኢንቨስትመንትና በንግድ ዘርፍ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ የተቻለበት ነው— የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ ) የተጠናቀቀው የ2012 ዓ.ም በኢንቨስትመንት እና በንግድ ዘርፍ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ የተቻለበት ዓመት እንደነበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

በአዲሱ ዓመት ከኢንቨስትመንትና ንግድ ዘርፎች በተጨማሪ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በቱሪዝም ዘርፎች ውጤት ለማምጣት ዝግጅት መደረጉም ተጠቁሟል።

አዲስ ዓመትን አስመልክቶ መልካም ምኞታቸውን የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ጽዮን ተክሉ÷ የተገባደደው 2012 ዓ.ም በፈተናዎች የተሞላ ቢሆንም የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።

ሚኒስቴሩ በኢንቨስትመንት፣ በንግድ፣ በቱሪዝምና በቴክኖሎጂ ሽግግር አንጻር የሚሰራቸውን የውጭ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ለማሳካት ጥረት ማድረጉን ጠቁመዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮናቫይረስ  ወረርሽኝ ሁሉንም አካል በተለያየ መንገድ በመንካት አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩንም አስታውሰዋል።

 

በቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ የሚያጋጥሙ ማነቆዎችን በመፍታት ረገድ የተሻለ ውጤት እንደተመዘገበ ወይዘሮ ጽዮን ተናግረዋል።

የውጭ ኢንቨስትመንት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የጀመረበት ጊዜ ቅርብ በመሆኑ የተለያዩ ችግሮች እንደሚያጋጥሙ ገልጸው ÷ በኢንቨስትመንት ላይ ከሚሰሩ ተቋማት፣ ከኤምባሲዎችና ከኢንቨስተሮች ጋር በመነጋገር ማነቆዎችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለው ቀውስና በንግድ ላይ ያሳረፈው ጫና የበረታ ቢሆንም በኢትዮጵያ የወጭ ንግድ አፈጻጸም መልካም እንደነበረ ሚኒስትር ዴኤታዋ አስታውሰዋል።

በተለይም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የነበረውን ብቃት ተጠቅሞ የሠራው ሥራ የሚደነቅ እንደሆነ  ተናግረዋል።

አያይዘውም ከተለያዩ ማኅበራት ጋር በመነጋገር የምርት መዳረሻ ትኩረትን በመለየት የተሰራው ሥራና የአገሪቱ ዲፕሎማቶች ጥረት ለወጭ ንግዱ ስኬት አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል።

በሌላም በኩል በ2012 ዓ.ም በቴክኖሎጂ ሽግግር የተወሰነ መዳከም እንደነበረ የተናገሩት ወይዘሮ ጽዮን ÷የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በስፋት ለመንቀሳቀስ አላስቻለም  ብለዋል።

ሆኖም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጉ ቴክኖሎጂዎችን የመለየትና የመምረጥ ሥራ መሥራታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም በቀጣይ ዲፕሎማቶች የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማረጋገጥ ምን ሊሰሩ እንደሚችሉ የመለየት ተግባር መከናወኑን ጠቁመዋል።

በቴክኖሎጂ ወደኋላ መቅረትን ወደ ዕድል መቀየር የምንችለውና ቴክኖሎጂዎችን ለእኛ አገር ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው የሚለውን መረዳት ላይ ተግባብተናል ብለዋል።

ከዚያም ባለፈ በቱሪዝም ዘርፍ በ2013 ዓ.ም በስፋት ለመሥራት የሚያስችል መሠረት መጣሉን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታዋ÷ ‘ጤና ይስጥልኝ’ የሚል ዘመቻ እንደሚጀመር መናገራቸውን ኢዜአ  ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.